ሽንዞ አቤን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ የአዕምሮ ጤና ምርመራ ሊደረግለት ነው
ግድያውን በመፈጸም የተጠረጠረው ግለሰብ ወዲያው መያዙ ይታወሳል
ሸንዞ አቤ የተገደሉት በጃፓን ለሚካሄደው ምርጫ ለገዥው ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ ነበር
የቀድሞውን የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤን በመግደል የተጠረጠለው ግለሰብ የአዕምሮ ምርመራ ሊደረግለት ነው፡፡
የሽንዙ አቤ ገዳይ የህክምና ምርመራ እንደሚደረግለት የጃፓን መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር በፈረንጆቹ ሃምሌ ስምንት ቀን 2022 ከአንድ ግለሰብ በተተኮሰ ጥይት ተመተው ሆስፒታል ገብተው መሞታቸው ይታወሳል።
ሺንዞ አቤ በምዕራባዊ ጃፓን በሚገኝና ናራ በተባለ ከተማ ጎዳና ላይ ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ከበስተጀርባቸው በተተኮሰ ሁለት ጥይት ደረታቸውን ተመተው ሆስፒታል ገብተው ነበር ያረፉት።
የዓለም ሚዲያዎች ሽንዙ አቤ ለህይወታቸው በሚያሰጋ የጤና ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን ከዘገቡ በኋላ ነበር ህልፈታቸው የተሰማው።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የ41 ዓመቱ የግድያ ሙከራው ፈጻሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን የገለጹ ሲሆን አሁን ደግሞ የህክምና ምርመራ ይደረግለታል እያሉ ነው።
አቤ በተመቱበት ጊዜ ለሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳን በማድረግ ላይ ነበሩ።
"አቤኖሚክስ" በሚባል የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና የሚታወቁት ሺንዞ በጃፓን የመሪነት ታሪክ ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ቀዳሚው ሰው ናቸው።አቤ ከሁለት ዓመታት በፊት ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትርነት መልቀቃቸው ይታወሳል።
ሸንዞ አቤ የተገደሉት በጃፓን ለሚካሄደው ምርጫ ለገዥው ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ ነበር፡፡