የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያደርግ ነው
ኢሰመኮ ታህሣሥ 16 ባወጣው መግለጫ የበኩጂ ሟቾች ቁጥር 207 መድረሱን መግለጹ ይታወሳል
በመተከል ዞን በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ የጉባዔው ዋነኛ ትኩረት ነው
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ፣ እንዳሉት ምክር ቤቱ በነገው ዕለት ታህሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በአሶሳ ከተማ አስቸኳይ ጉባዔውን ያካሂዳል። በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ፣የጉባኤው ትኩረት እንደሚሆን ነው ምክትል አፈጉባዔዋ ያስታወቁት፡፡
ምክር ቤቱ ከመተከል ዞን የዜጎች ጭፍጨፋ ባለፈም በሌሎች ክልላዊ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ገለጸዋል፡፡ ከሰሞኑ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከ200 በላይ ንጹሃን በማንነታቸው ተለይተው መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ሲሆን በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለውን ይህንን ጭፍጨፋ ለማስቆም መንግስት የጸጥታ ኃይል መላኩን መግለጹ ይታወሳል፡፡
በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ታህሣሥ 16 አስታውቋል። በንጹሃን ላይ ማንነትን መሰረት ያረገው ግድያ የተፈጸመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓዊ ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገው በተመለሱ ማግስት ነበር፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ “ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት ያደረግነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም” ካሉ በኋላ “መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ብለዋል። “የጠላቶቻችን ዓላማ በጁንታው ላይ የሠነዘርነውን ብርቱ ኃይል ለመበተን ነው። ይህ የሚሳካ አይደለም” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረትና በኅብረት መስራት አለበት ማለታቸውም ይታወሳል፡፡