በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ተወሰነ
በዞኑ በተመሰረቱት ካምፖች ለሚገኙ ወገኖች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ እርዳታዎች የተከፋፈሉ ሲሆን ተጨማሪ እርዳታዎችን የጫኑ መኪኖች ወደቦታው ተንቀሳቅሰዋልም ተብሏል
የማዕከሉን ተግባራት የሚያስተባብሩ የሰላም ሚኒስቴር ግብረ ኃይል አባላት ዞኑ ማቅናታቸውም ተነግሯል
ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ዘር ተኮር ጥቃቶች በተፈጸሙበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡
ማዕከሉ እንዲቋቋም የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ነው፡፡
ኮሚቴው ስር የሰደደውን የመተከሉን ጥቃት ተቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ በህግ ማስከበር ሂደቱ ላጋጠሙ ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን የገመገመበትን መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።
በስብሰባውም በመተከል የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ በኋላ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች የነበረውን ሰላም ወደ ቀደመ ይዞታው የመመለስ እና በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ተግባራትም በኮሚቴው ተገምግመዋል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ አካላትን የያዙ ቡድኖች በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር ክልሎች እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ያደረጉትን የመስክ ምልከታ መሰረት ያደረገ ቀጣይ አቅጣጫም ተቀምጧል።
በብሄራዊ አደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን አስተባባሪነት በቅርቡ በመተከል ዞን በተመሰረቱት ካምፖች ለሚገኙ ወገኖች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ እርዳታዎች የተከፋፈሉ ሲሆን ተጨማሪም እርዳታዎችን የጫኑ መኪኖች ወደቦታው ተንቀሳቅሰዋል ተብሏል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር ዴኤታዎች የሚመራ የአመራሮች እና የባለሙያዎች ግብረ ኃይል ወደ መተከል ዞን መጓዙንም ከሰላም ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡