በቤኒሻንጉል “መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ጠ/ሚ ዐቢይ
ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ጸረ-ሠላም የተባሉ 42 ሰዎች መደምሰሳቸው ተገልጿል
ጠ/ሚኒስትሩ “ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት ያደረግነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም” ብለዋል
በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ውስጥ “በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል” ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ “በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ” በማለት በስፍራው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገው በተመለሱ ማግስት በተፈጸመው ጭፍጨፋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ “ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት ያደረግነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም” ካሉ በኋላ “መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ብለዋል። “የጠላቶቻችን ዓላማ በጁንታው ላይ የሠነዘርነውን ብርቱ ኃይል ለመበተን ነው። ይህ የሚሳካ አይደለም” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረትና በኅብረት እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል።
ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትናንትናው ዕለት ገልጿል፡፡ ይህም በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
በርካታ ቤቶች እና የደረሱ ሰብሎች በእሳት ስለመጋየታቸውም የገለጸው ኮሚሽኑ ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል ብሏል።
የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በትናንትናው ዕለት በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ መከላከያ ሰራዊት ተከታትሎ በወሰደው እርምጃ 42ቱ መገደላቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን እንዳስታወቀው የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃም ጸረ-ሠላም ኃይሎች ለጥፋት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና እና ቀስቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።