ከሰሞኑ በውሰት ባመራበት ሌላኛው ጁቬ ስታቢያ ክለብ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ደጋፊዎች የቅም አያቱን ፋሺስት ምልክት እያሳዩ ደስታውን ተጋርተዋል
እግር ኳስ ተጫዋቹ የቤኒቶ ሞሶሎኒ የልጅ ልጅ
ቤኒቶ ሞሶሎኒ ጣልያናዊ ፖለቲከኛ ሲሆን ሀገሪቱን ከፈረንጆቹ 1922 እስከ 1943 ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅትም ጦራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው በቅኝ ግዛት እንዲያስተዳድሩ ያደረጉት ሙከራ በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ጣልያን በአፍሪካ እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ አዋርደዋል በሚል ጥርስ የተነከሰባቸው ሞሶሎኒ በመጨረሻም ከባለቤታቸው ጋር ወደ ስዊዘርላንድ ሊያመልጡ ሲል ከተያዙ በኋላ በ1945 በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል፡፡
ከሞሶሎኒ የዘር ተዋረድ ያለው ሮማኖ ፍሎሪያኒ በጣልያን መዲና ሮም እግር ኳስ አካዳሚ ያደገ ሲሆን ለላዚዮ ክለብ ፈርሟል፡፡
ይህ እግር ኳስ ተጫዋች ከላዚዮ በውሰት ጁቬ ስታቢያ ለተሰኘው ክለብ እየተጫወተ ይገኛል፡፡
በሀገሪቱ ሁለተኛ ሊግ እየተወዳደረ ለሚገኘው ጁቬ ስታቢያ 16 ጨዋታዎችን ያደረገው ይህ ተጫዋች ከሰሞኑ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
ክለቡ ጁቬ ስታቢያ ከሴሴና ጋር ያደረገውን ጨዋታም በሮማኖ ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ችሏል ተብሏል፡፡
ሮማኖ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ወደ ደጋፊዎች በመቅረብ እጁን አፉ ላይ አድርጎ ያያቸው ሲሆን ደጋፊዎች ደግሞ የሮማኖ ቅመ አያት እና የቀድሞ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒቶ ሞሶሎኒ ምልክት የሆነው የፋሺስት ምልክትን አሳይተዋል ሲል የጣልያን ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በጣልያን ፋሺስት ፓርቲ ማቋቋምን በይፋ በህግ ያገደች ሲሆን ምልክቱን መጠቀም ግን አልከለከለችም፡፡