እስራኤል ፓርላማዋን በተነች
ፓርላማው የተበተነው በኔታንያሁ በሚመራው ‘ሊኩድ’ ፓርቲ እና በቤኒ ጋንዝ ‘ብሉ ኤንድ ኋይት’ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረው ሊታረቅ ያልቻለ የጎላ ልዩነት ምክንያት ነው ተብሏል
በሁለት ዓመታት ውስጥ 4ኛውን ምርጫ በመጪው መጋቢት ታካሂዳለች ተብሏል
የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) በመሪ የሃገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሊታረቅ ያልቻለ ልዩነት ምክንያት ተበተነ፡፡
ፓርላማው የተበተነው በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሚመራው ‘ሊኩድ’ ፓርቲ እና በተቀያሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ‘ብሉ ኤንድ ኋይት’ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረው ሊታረቅ ያልቻለ የጎላ ልዩነት ምክንያት ነው፡፡
በዚህም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተቀምጦ የነበረው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ላይ መበተኑ ይፋ ሆኗል፡፡
በፈረቃ ስልጣን ሊይዙ ከሚችሉበት ስምምነት ደርሰው ባሳለፍነው ግንቦት መንግስት የመሰረቱት ፓርቲዎቹ በዓመታተዊው የመንግስት በጀት ላይ ሊስማሙ አልቻሉም፡፡
መንግስት በተመሰረተ 100 ቀናት ውስጥ በጀት ሊጸድቅ መቻል እንዳለበት የሃገሪቱ ህግ ያትታል፡፡ ይህም እስካሳለፍነው ወርሃ ነሃሴ አጋማሽ ማለት ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያች እየተገፋ በጀቱን ለማጽደቅ የሚያስችለው ውሳኔ ሳይተላለፍ ፓርላማው መበተኑ እስከተነገረበት ዕለት ድረስ ዘልቆ ነበረ፡፡
እንደ ሚድል ኢስት ሞኒተር ከሆነ ኔታንያሁ ሊጠናቀቅ ለታቀረበት የፈርንጆቹ ዓመት 2020 የተያዘው በጀት እንዲጸድቅ ጽኑ ፍላጎት አላቸው፡፡ ጋንዝ እና ፓርቲያቸው ደግሞ ከአሁን ቀደም በተስማማነው መሰረት በጀቱ የመጪውን ዓመት (2021) አካቶ መጽደቅ አለበት በሚል ይሞግታሉ፡፡
ይህ ልዩነታቸው ሊታረቅ ሳይችል ቀርቶም በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ነው ወደ ተባለለት ምርጫ ለማምራት ተገደዋል፡፡ ምርጫው ከሶስት ወር በኋላ በወርሃ መጋቢት መጨረሻ አካባቢ እንዲካሄድም ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡
ፓርቲዎቹ እርስ በእርስ እየተወቃቀሱ ነው፡፡ አንዱ በአንዱም ላይ ይጠቋቆማል፡፡ ኔታንያሁ ተቀናቃኞቻቸውን ወቅሰው በምርጫው ለማሸነፍ ዝተዋል፡፡
ጋንዝ ደግሞ በኔታንያሁ እና በፓርቲያቸው ምክንያት በጀቱ ሳይጸድቅ ለ6 ወራት መጓተቱን በመጠቆም ይህን ያደረጉት በደረስነው ስምምነት መሰረት ስልጣን ላለማጋራት ነው ሲሉ ከስሰዋል፡፡
ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰጡት ምላሽ ወቀሳ የበዛባቸው ኔታንያሁ ከፍተኛ ህዝባዊ ጫና አለባቸው፡፡ ሆኖም በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ስምምነት ስም ከተለያዩ የአረብ ሃገራት ጋር ያደረጉት ስምምነት በምርጫው ትልቅ ተስፋን ሊሰጣቸው እንደሚችል ይታሰባል፡፡