ቤንዜማ እስራኤልን በመቃወሜ ስሜን አጉድፈውታል ያላቸውን የፈረንሳይ ሚኒስትር ከሰሰ
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ቤንዜማ "ከሙስሊም ወንድማማች ቡድን ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው” ማለታቸው ይታወሳል
የተጫዋቹ ጠበቃ የሚኒስትሩ አስተያየት “የቤንዜማን ክብርና ዝና ጎድቷል” ብለዋል
ፈረንሳዊው ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ላይ ክስ መሰረተ።
ቤንዜማ በህዳር ወር አጋማሽ እስራኤል በጋዛ የምትፈፅመውን የቦምብ ጥቃት መቃወሙ ይታወሳል።
የ2022 የባሎንዶር አሸናፊው በኤክስ ገፁ ያሰፈረውን መልዕክት ተከትሎም የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን ቤንዜማ "ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው" የሚል አስተያየት መስጠታቸው አይዘነጋም።
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ጠበቃ ሁጌስ ቪጊር ይህ የሚኒስትሩ አስተያየት የቤንዜማን ክብርና ዝና መጉዳቱን ተናግረዋል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተመለከተው ክስ ቤንዜማ "ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም፤ የድርጅቱ አባል የሆነ ሰውም አላውቅም" ማለቱን ይጠቅሳል።
በሚኒስትሩ ላይ በቀረበው የስም ማጥፋት ክስ ተጫዋቹ "በጋዛ እየተፈፀመ ያለው ድርጊት ከዚህ በበለጠ እንጂ ባነሰ መልኩ ሊገለፅ እንደማይችል ይታወቃል፤ ነገር ግን እኔን የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ አድርገውኛል" ሲል መግለፁም ተመላክቷል።
የፈረንሳዩ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ግን ተጫዋቹ በሀማስ ጥቃት ለተገደሉ እስራኤላውያንም ሆነ በቀድሞ አክራሪ ተማሪዋ ለተገደለችው ፈረንሳዊት መምህር ድምፅ መሆን አለመቻሉ ትዝብት ውስጥ እንደሚጥለው መናገራቸው ይታወሳል።
ቤንዜማ በሽብርተኛ ስለተገደለችው መምህርት በኤክስ ገፁ እንዲፅፍ በቀጥታ ብጠይቀውም አላደረገውም ያሉት ዳርማኒን፥ ተጫዋቹ የፈሰንሳይ ብሄራዊ ቡድን መዝሙር ለመዘመር አይፈልግም የሚል ወቀሳንም ሲያቀርቡበት ነበር።
ካሪም ቤንዜማ ከትውልደ አልጀሪያውያን ወላጆቹ በፈረንሳይ ሊዮን በፈረንጆቹ 1987 ነው የተወለደው።
የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ኮከቡ ቤንዜማ በሪያል ማድሪድ የ14 አመት ቆይታው አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ፣ አራት የላሊጋ እና ሶስት የኮፓዴላሬ ዋንጫዎችን አንስቶ ወደ ሳኡዲው ክለብ አል ኢትሃድ አቅንቷል።