የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ያላቸው ቅርርብ መጠናከሩን አስታወቁ
ሲልቪዮ ቤርልስኮኒ ፓርቲያቸው በቅርቡ በጣልያን በተካሄደው ምርጫ ድል የቀናው መሆኑ ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለቀድሞው የጣልያን መሪ 20 የሩሲያ ቮድካ የልደት ስጦታ መላካቸው ተገልጿል
የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መቀራረባቸውን ተናገሩ።
ጣልያንን ለዘጠኝ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ነጋዴው እና ፖለቲከኛው ሲልቪዮ ቤርልስኮኒ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የበለጠ መቀራረባቸውን ተናግረዋል።
የፎርዛ ኢታሊያ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቤርሊስኮኒ በቅርቡ በተካሄደው የጣልያን ምክር ቤት ምርጫ መቀመጫዎችን የሸነፉ ሲሆን፤ ከሌሎች ፓርተሪዎች ጋር በመተባበር መንግስት እንደሚመሰርቱ ይጠበቃል።
ቤርሊስኮኒ እንዳሉት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የበለጠ እየተቀራረቡ መሆኑን የጣልያን ፕረስ ኤጀንሲ በድብቅ የተቀረጸ የድምጽ ቅጂን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የቤርሊስኮኒ አስተያየት በቅርቡ የሚመሰረተው አዲሱ የጣልያን መንግስት ከሩሲያ ጋር ቅርበት ያለው ሊሆን ይችላል በሚል ከዚህ በፊት በአውሮፓ ህብረትን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራትን የተነሳውን ስጋት የበለጠ እንዳሰፋው ተገልጿል።
ቤርሊስኮኒ በዚህ በድብቅ በተቀረጸው የድምጽ ቅጂ ንግግራቸው" ከቭላድሚር ፑቲን ጋር እየተቀራረብኩ ነው፣ ለልደቴም 20 ቮድካዎችን እና ደብዳቤ ልኮልኛል፣ እኔም በምትኩ ለወዳጄ ፑቲን 20 የጣልያን ቀይ ወይን እና ደብዳቤ ልኬለታለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል ተብሏል።
የስድስት ቢሊዮን ዶላር ባለጸጋ የሆኑት የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሊቪዮ ቤርሊስኮኒ ባሳለፍነው መስከረም 29 ላይ 86ኛ ዓመታቸውን አክብረዋል።
ቤርሊስኮኒ አክለውም ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ለፈጸሙት ወንጀል ይቅርታ አድርጌላቸዋለሁ ምክንያቱም ምዕራባዊያን ለዩክሬን ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ ስለሆነ ሲሉም ተናግረዋል ተብሏል።
ፓርቲያቸው ፎርዛ ኢታሊያ ዘገባውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ፓርቲው ከአውሮፓ እና አሜሪካ ጎን መሆኑን አስታውቋል።
የጣልያን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ድራጊ በሀገሪቱ ምክር ቤት መተማመኛ ድምጽ መነፈጋቸውን ተከትሎ በቅርቡ አዲስ የምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል።
በዚህ ምርጫ ላይ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች አብላጫውን የህግ አውጪ ምክር ቤት መቀመጫ የያዙ ሲሆን የጣልያን ቀኝ ክንፍ ወንድማማቾች ፓርቲ መሪ የሆኑት ጆርጂያ ሜሎኒ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይጠበቃል።