አሜሪካዊው ሴናተር ሳንደርስ፤ ሀገራቸው ከቻይና ጋር ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት እንዳትገባ አሳሰቡ
አሜሪካን ጨምሮ የቡድን 7 አባል ሀገራት እያደገ የመጣውን የቻይና ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል ያሉትን እቅድ ማውጣታቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው
አሜሪካ ችግሮችን ለመፍታት ቻይናንም አጋር ማድረግ አለባት ብለዋል ሴናተሩ
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ የነበሩት በርኒ ሳንደርስ አሜሪካ፤ ከቻይና ጋር ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት እንዳትገባ አሳሰቡ፡፡
ሴናተር ሳንደርስ፤ ፎሬይን አፌርስ መጽሄት ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ ዋሸንግተን፤ ቤጅንግን የህልውናዋ ጠላት አድርጋ ከማየት መቆጠብ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የኒዩክለር ማብለያ ጣቢያዎች መስፋፋት፣ ሽብርተኝነት፣ የኢኮኖሚ አለመመጣጠንና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉባት ገልጸው ችግሮቹን ግን ብቻዋን መቋቋም እንደማትችል አንስተዋል፡፡ በመሆኑም የዓለም የጋራ የሆኑት እነዚህና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት አሜሪካ፤ ቻይናንም አጋር አድርጋ መንቀሳቀስ እንዳለባት አሳስበዋል፡፡ አሁን ላይ በዓለም ላይ ትብብር እጅጉን እንደሚያስፈልግ ያነሱት ሳደርስ ቤጅንግን ጨምሮ ሌሎች አጋሮችም እጅጉን አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት አሁን ላይ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ሽኩቻዎች የዜሮ ድምር ደረጃ ላይ እንደደረሰ በዋሸንግተን በኩል አቋም በመያዝ ላይ መሆኑ አደገኛ እንደሆነም ሳንደርስ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ሁለቱም ፓርቲዎች (ዴሞክራት እና ሪፐብሊካን) ፤ ከ20 ዓመት በፊት ቻይናን በቋሚነት የአሜሪካ የንግድ አጋር አድርገው ይመለከቷት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ያለው የኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ሽኩቻ ዓለም የገጠመውን ችግር በጋራ ለመፍታት እንደማያስችል ገልጸዋል፡፡
ከቀናት በፊት የቡድን 7 አባል አገራት በእንግሊዝ ኮርንዌል የባህር ዳርቻ ከተማ ባካሄዱት ዓመታዊ ጉባዔ ቻይናን ዋነኛ ጉዳያቸው አድርገው ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ እያደገ የመጣውን የቻይና ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል ያሉትን እቅድ ማውጣታቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም አሜሪካ ግን ዕቅዱ “የቻይናን ተጽዕኖ ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር ያለመ ነው” ማለቷ አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ባለፈም አሜሪካ፤ ቻይና በአፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ ለመቀማት ያለመ ዕቅድም መንደፏ መገለጹም ይታወሳል፡፡
ቻይና በበኩሏ ዓለም በጥቂት ቡድኖች ሊመራ እንደማይችል በመግለጽ የአባል ሀገራቱን ዕድቅ ውድቅ አድርጋለች፡፡
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ተካሮ የነበረው የቤጅንግና የዋሸንግተን ሁሉን አቀፍ እሰጥ አገባ በዘመነ ባይደን አስተዳደርም መቀጠሉን ምልክቶች ያሳያሉ፡፡