የቡድን 7 አባል አገራት “የቻይናን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል”ያሉትን አዲስ እቅድ ይፋ አደረጉ
ቻይና እስካሁን የቡድኑ አባል ሃገራት አዘጋጅተናል ስላሉት አዲስ እቅድ ያለችው ነገር የለም
አሜሪካ እቅዱ የቻይናን ተጽዕኖን ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር ያለመም ነው ብላለች
የቡድን ሰባት አባል አገራት በእንግሊዝ ኮርንዌል የባህር ዳርቻ ከተማ ዓመታዊ ጉባዔያቸውን አካሂደዋል።
በጉባዔው የአዘጋጇን የእንግሊዝን ጨምሮ የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈውበታል።
የዚህ የዓለማችን ባለጸጋ አገራት ስብስብ የስብሰባ አጀንዳ የኮሮና ቫይረስ እና የአየር ንብረት ነው ይባል እንጂ ዓለማችንን በቀዳሚነት ለመቆጣጠር እየገሰገሰች ያለችው የሩቅ ምስራቋ ቻይና ጉዳይ ዋነኛ ትኩረታቸው ነበረች።
ቻይና በፍጥነት እያደገች ያለች አገር ስትሆን በተለይም በፈረንጆቹ 2013 ዓመት ይፋ ያደረገችው የ“ቤልት ኤንድ ሮድ” ማዕቀፍ ምዕራባዊያንን አስደንግጧል።
ይህ ዓለም አቀፍ እቅድ ቻይና ከእስያ፣ ከአውሮፓ እና ከተቀረው ዓለም ጋር በትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች በመተሳሰር የተሻለ ዓለምን መፍጠር አላማው አድርጎ መጀመሩን በወቅቱ የቻይናው ፕሬዘዳነት ሺ ጂንፒንግ ተናግረው ነበር።
ይህ ፕሮጀክት ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ በሆነ በጀት ከ2 ሺህ 500 በላይ የመሰረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑ ተገልጽል።
ይህ እቅድ ለረጅም ጊዜ የአሜሪካ እና ምዕራባዊያን አገራት ወዳጅ የነበሩትን አገራት ትኩረት ወደ ቻይና እንዲያዞሩ ማድረጉ ሲገለጽ ቆይቷል።
የቡድን ሰባት አገራት ደግሞ “የተሻለ ዓለም የመፍጠር እቅድ” የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ እቅድ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር 2035 ዓመት የመሰረተ ልማት ችግራቸውን ለመፍታት 40 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋቸዋል በሚል ለተቀመጠው ስጋት ምላሽ ለመስጠት ዓላማው እንደሆነ የአሜሪካ የነጩ ቤተመንግስት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይሁንና ይህ የቡድን ሰባት አገራት አዲስ እቅድ ባለፉት 40 ዓመታት በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በፍጥነት እያደገች ለመጣችው ቻይና ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው የሚል ሀሳብ እየቀረበበት ይገኛል።
የፕሬዝዳንት ባይደን ከፍተኛ ሀላፊ እንዳሉት “ይህ እቅድ የተነደፈው የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት አይደለም እቅዱ ዓለማችን ለሚገጥማት ችግር አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ነው” ማለታቸውን ሮይተረስ በዘገባው ጠቅሷል።
የቡድን ሰባት አገራት በዚህ እቅድ መነሻነት ከቻይና ጋር በጋራ መስራት ከሚችሉባቸው ጉዳዮች መካከል የንግድ እና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ዋነኞቹ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በዚህ እቅድ መሰረትም የቡድን ሰባት አገራት የዓለማችንን ባለሀብቶች በማስተባበር በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጾታ እኩልነት እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት ዙሪያ እንደሚሰሩም ተገልጿል።
ይሁንና ይህ እቅድ እንዴት እንደሚተገበር እና ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገው እስካሁን አልተጠቀሰም።
ከ8 ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው የቻይናው ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺዬቲቭ እስካሁን ከ100 በላይ አገራት የፈረሙት ሲሆን ቻይና ለብዙ አገራት የባቡር፣ ወደብ፣ አውሮፕላን ጣቢያ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎችን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ የገንዘብ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረጓ በዘገባው ተገልጿል።
ቻይና ከዛሬ 42 ዓመት በፊት ያላት ኢኮኖሚ ከጣልያን ኢኮኖሚ ያንስ የነበረ ሲሆን አገሪቱ ኢኮኖሚዋን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት ካደረገች በኋላ ግን በፍጥነት ማደግ ችላ አሁን ላይ ሁለተኛዋ የዓለማችን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ አገር ሆናለች።
ቻይና በቡድን ሰባት አገራት ይፋ የተደረገውን ይህን እቅድ አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን በቀጣይ ቀናት ስለ እቅዱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ምላሽ እንደምትሰጥ ይጠበቃል።