ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጣልቃገብነት “በፍጹም ተቀባይነት የለውም” አለች
አሜሪካ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በባለስልጣናት ላይ የጉዞ እግድ ለመጣል መዘጋጀቷን ገልጻለች
ሚኒስቴሩ የአሜሪካ የጉዞ እገዳ ምርጫ ለማድረግ በምትዘጋጀው ኢትዮጵያ ላይ “የተሳሳተ መልእክት” ያስተላልፋል ብሏል
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት በተደጋጋሚ የምታደርገው ሙከራ ተገቢ አይደለም፤ በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ ለትግራይ ክልል ግጭት ኃላፊነት አለባቸው ባላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ የአማራ ኃይሎች፣ የህወሓት አባላት ላይ የጉዞ እግድ ለመጣል መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳይ እንዴት መምራት እንዳለባት ሊነገራት እንደማይገባ አመልክቷል፡፡ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ላላት ታሪካዊ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ያመለከተው መግለጫው የጉዞ እገዳ መጣልና ሌሎች ተዛማጅ እርምጃች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በእጅጉ እንደሚጎዳ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የአሜሪካ መንግስት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር በእኩል ደረጃ ማየቱ እንዳሳዘነውና ይህም የአሜሪካን አስተዳደር የተሳሳተ አካሄድ ያሳያል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ብሄራዊ ንግግር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለጸው መግለጫው “ነገርግን በሽብር ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ቁጭ ብሎ ለመነጋጋር ሊገደድ አይችልም፤ህወሓት እንዲያንሰራራ ለማድረግ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አፍራሽ ነው” ብሏል መግለጫው፡፡
በትግራይ አለ የተባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትን በሚመለከትም ፣ መንግስት ለጥሰቱ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው ያላቸውን ተጠያቂ ለመድረግ ቁርጠኛ ነው፣ ጠቅላይ ኣቤ ህግም በመብት ጥሰት የተሳተፉትን ለመለየት ምርመራ ማካሄዱን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመግለጫው መንግስት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ኮሚሽን የመብት ጥሰትን መመርመር ጀምረዋል ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት “በምርጫው ላይ ጥላ የሚያጠላ የተሳሳተ ውሳኔ አይጠብቅም” ብሏል
በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ በማውጣት በኢትዮጵያ ላይ ከመጠን በላይ ጫና ማሳደርን ለመቀጠል አሜሪካ የወሰደችውን እርምጃ አሳዛኝ ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል፡፡
የአሜሪካን የቪዛ እገዳ ውሳኔ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ይህ የቪዛ እገዳ ውሳኔ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ኢኮኖሚያዊና የደህንነት ድጋፍ ለማቋረጥ ከዚህ በፊት ካወጣችው ውሳኔ በተጨማሪ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ይህ ውሳኔ የመጣው “የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር አወንታዊ እና ገንቢ በሆነ መልኩ እየተሳተፈ ባለበት ወቅት ነው” ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አግኝተው ሰፊ ምክክር ያደረጉትን አዲሱን የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን ኢትዮጵያ መቀበሏንም ነው መግለጫው የጠቀሰው፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ ውሳኔ ፣ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ዘመን ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ ሀገሪቱ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት “የተሳሳተ መልዕክት ይኖረዋል” ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ 6 ኛው ብሔራዊ ምርጫ ፣ አዲስ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ “ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ይከፍታል” ሲልም ነው የጠቆመው፡፡ ስለሆነም በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፎችን እና መረዳቶችን እንጂ “በምርጫው ላይ ያለአግባብ ጥላ የሚያጠላ የተሳሳተ ውሳኔአይጠብቅም” ሲል ገልጿል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር ተከታታይ ንግግሮች ተደርገው ለችግሮች ተጨባጭ ምላሽ መስጠት በተጀመረበት በዚህ ወቅት የጉዞ እገዳን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ መወሰኑ የሚያስቆጭ ብቻም ሳይሆን ከአሁን ቀደም የነበሩ ገንቢ የግንኙነት መንገዶችንና የተገኙ ውጤቶችን፤ ለዘመናት የዘለቀውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ጭምር ክፉኛ ከመጉዳትም በላይ ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነም ገልጿል፡፡
መግለጫው በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብ የሆኑና ያለንን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዝቅ ያደረጉ ውሳኔዎች የማይቆሙ ከሆነ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ከሁለትዮሽ የተሻገረ አንድምታ ያለውን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን ትገደዳለችም ነው ያለው፡፡
በውሳኔው ተስፋ ሳይቆርጥ ችግሮችን ለመፍታትና ሃገሪቱን ወደ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ጎዳና ለመምራት ሳይታክት እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው፡፡
ትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ክልሉን ሲመሩ የነበሩ የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
በክልሉ ግጭቱን ተከትሎ የንጹሃን ግድያና ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች መፈጸማቸው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ና በተለያዩ የአለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መጥቀሱ ይታወሳል፡፡