“ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰኑበት ጊዜ አብቅቷል”- ለቡድን 7 ሀገራት የቻይና ምላሽ
የቡድን 7 ሀገራት “የቻይናን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል” ያሉትን እቅድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል
በዩኬ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ቡድን 7 በቻይና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም አሳስበዋል
የቡድን 7 ሀገራት በዩናይትድ ኪንግደም ያካሔዱትን ስብሰባ ተከትሎ የቻይናን የኢኮኖሚ ግስጋሴ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ለመግታት ያስችለናል ያሉትን የጋራ እቅድ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ቻይና ለዚህ የባላንጣዎቿ እቅድ በሰጠችው ምላሽ “የጥቂት ሀገራት ቡድን በዓለም ጉዳዮች ላይ በብቸኝነት የሚወስንበት ጊዜ አብቅቷል” ብላለች።
በዩኬ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃለ አቀባይ "ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች በጥቂት ሀገራት ቡድን የሚወሰኑበት ጊዜ አልፏል” ያሉ ሲሆን፣ አክለውም “እኛ ሁልጊዜም ትልቅም ሆኑ ትንሽ፣ ደሀም ሆኑ ሀብታም፣ ጠንካራም ሆኑ ደካማ ሁሉም ሀገራት እኩል ናቸው ብለን እናምናለን፤ የዓለም ጉዳዮች ሁሉንም ሀገራት ባማከለ መልኩ ሊወሰኑ ይገባል” ብለዋል።
የቡድን ሰባት ሀገራት የቻይናን የ “ቤልት ኤንድ ሮድ” መርሀግብር ለመቋቋም “የተሻለ ዓለም መፍጠር” የተሰኘ አዲስ እቅድ ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ እቅድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በፈረንጆቹ 2035 የመሰረተ ልማት ችግራቸውን ለመፍታት 40 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋቸዋል በሚል ለተቀመጠው ጥናታዊ ሀሳብ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ የቡድን ሰባት አገራት አዲስ እቅድ ባለፉት 40 ዓመታት በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በፍጥነት እያደገች ለመጣችው ቻይና ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው ቢባልም፣ የፕሬዝደንት ባይደን ከፍተኛ አማካሪ “የዚህ እቅድ ዓላማ ዓለማችን ለሚገጥማት ችግር አዎንታዊ ሚና ለመስጠት ነው” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቡድን ሰባት (G7) መሪዎች የቻይናን ሆንግ ኮንግ ልዩ የአስተዳደር ክልል ፣ የዢንጂያንግ ኡይጉርን የራስ ገዝ አስተዳደር እና ታይዋንን በሚመለከት ያወጡትን የጋራ መግለጫም በዩኬ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ተችተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ “የቡድን 7 ትችት የተዛቡ እውነታዎችን መሠረት ያደረገ” መሆኑን በመግለጽ ቡድን 7 በቻይና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም አሳስበዋል፡፡
“አሜሪካ እና ሌሎች የ ቡድን 7 አባላት እውነታዎችን እንዲያከብሩ ፣ በሀሰት የቻይና ስም ከማጥፋት እንዲቆጠቡ፣ በቻይና የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትን እንዲያቆሙ፣ በቻይና ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረስ እንዲያቆሙ እንዲሁም ግጭት እና መቃቃር ከመፍጠር ይልቅ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲያደርጉ እናሳስባለን” ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
ቻይና “ከገበያ ውጭ” ፖሊሲዎችን እንደምትከተል ተደርጎ የሚቀርብባትን ክስ “ፍጹም ሀሰት” እንደሆነ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የቻይና አጠቃላይ የታሪፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. ከህዳር 2018 ጀምሮ ወደ 7.5 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ሀገሪቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንተርፕራይዞች በእኩልነት የሚስተናገዱበትን እና በእኩል ደረጃ የሚፎካከሩበትን የገቢያ ሁኔታ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የቡድን 7 ሀገራት በቻይና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይም መግለጫ በመስጠታቸው ነው ቃል አቀባዩ ከውስጥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሀገራቱን የተቹት፡፡