የአማዞን መስራቹ ጄፍ ቤዞስ የአለማችን ቁጥር 1 ቱጃር ሆነ
ቤዞስ በ200 ቢሊየን ዶላር ሀብት ነው ኤለን መስክን በመብለጥ የምድራችን ቀዳሚው ባለጠጋ የሆነው
የቢሊየነሮች ደረጃን እየተፈራረቁ የመሩት መስክ እና በርናርድ አርኖልት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል
አሜሪካዊው የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ጄፍ ቤዞስ የአለማችን ቁጥር አንድ ቱጃርነቱን ዳግም ያዘ።
የግዙፉ የኦንላንይን መገበያያ አማዞን መስራቹ ቤዞስ የቴስላ እና ኤክስ (ትዊተር) ባለቤቱን ኤለን መስክ በመብለጥ ነው ቀዳሚው ቢሊየነር የሆነው።
ብሉምበርግ በትናንትናው እለት ባወጣው የአለማችን ቢሊየነሮች ደረጃ መሰረት ጄፍ ቤዞስ በ200 ቢሊየን ዶላር ሀብት ይመራል።
በግንቦት ወር 2023 የአለማችን ቀዳሚው ባለጠጋነት ክብርን ይዞ የነበረው ኤለን መስክ በ198 ቢሊየን ዶላር ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የብሉምበርግ መረጃ እንደሚያሳየው መስክ ባለፈው አመት 31 ቢሊየን ዶላር ሲያጣ፥ የቤዞስ ሀብት በ23 ቢሊየን ዶላር ጨምሯል።
የቴስላ አክሲዮን ሽያጭም በትናንትናው እለት በ7 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ነው የተነገረው።
ዲዮር፣ ሴሊን እና ሊዩስ ቩይተን የተሰኙ ብራንድ ሽቶ እና ቦርሳዎችን የሚያመርተው የፈረንሳይ ኩባንያ ባለቤቱ በርናርድ አርኖልት ከኤለን መስክ በ1 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብለው ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የሜታ ባለቤቱ ማርክ ዙከርበርግ በ179 ቢሊየን ዶላር፤ የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ በ150 ቢሊየን ዶላር ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
የአለማችን የቢሊየነሮች ደረጃ በየወሩ ይለዋወጣል የሚለው ብሉምበርግ፥ ኤለን መስክ እና በርናርድ አርኖልት ከ2020 ጀምሮ ከፍተኛ ሃብት ያካበቱ ባለጠጎች መሆናቸውን ጠቅሷል።
የአለማችን አምስቱ ቀዳሚ ቢሊየነሮች ሃብት ከ2020 ወዲህ በ114 በመቶ አድጎ 869 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ነው የኦክስፋም አመታዊ የኢፍትሃዊነት ሪፖርት የሚያሳየው።
አሜሪካውያኑ ስቲቭ ባልመር፣ ዋረን ቡፌት፣ ሌሪ ኢሊሰን፣ ሌሪ ፔጅ እና ሰርጌ ብሪን ከ146 እስከ 113 ቢሊየን ዶላር ሃብት በማስመዝገብ ከ6ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።