ኤለን መስክ በድጋሚ የአለማችን ቀዳሚው ቱጃር ሆነ
መስክ በ192 ቢሊየን ዶላር ሃብት በፈረንሳዊው በርናልድ አርኖልት ተነጥቆ የነበረውን ደረጃውን አስመልሷል
የአማዞን መስራቹ ጄፍ ቤዞስ እና ቢል ጌትስ ሃብታቸውን ቢቀንስም ደረጃቸውን አስጠብቀዋል
የትዊተር፣ ቴስላ እና ስፔስኤክስ ባለቤቱ ኤለን መስክ ዳግም ወደ አለማችን ቀዳሚ ቱጃርነቱ ተመልሷል።
ብሉምበርግ ዛሬ ባወጣው የቢሊየነሮች ደረጃ መሰረት የመስክ አጠቃላይ ሃብት 192 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
ይህም የ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ጭማሪ ያሳየ ነው።
በአንጻሩ የቢሊየነሮቹን ደረጃ ከፊት ሲመሩ የቆዩት ፈረንሳዊው የቅንጡ እቃዎች አቅራቢ ድርጅት ባለቤቱ በርናርድ አርኖልት ሃብት ወደ 187 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል፤ የ5 ነጥብ 25 ቢሊየን ዶላር ቅናሹ ደረጃቸውን ለመስክ አሳልፈው እንዲሰጡ አድርጓቸዋል ነው የሚለው ብሉምበርግ።
አርኖልት የአለማችን አንደኛው ቱጃር ሲባሉ 211 ቢሊየን ዶላር ሃብት አስመዝግበው ነበር።
ኤልቪኤምኤች የተሰኘው ኩባንያቸው የአክሲዮን ዋጋ በ10 በሞ ሲቀንስም በአንድ ቀን ብቻ 11 ቢሊየን ዶላር ከሃብታቸው ላይ እንዳጡ ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የአማዞን መስራቹ ጄፍ ቤዞስ በ144 ቢሊየን ዶላር ሃብት አርኖልትን ተከትለው ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የማይክሮሶፍት ባለቤቱ ቢል ጌትስ በበኩሉ 125 ቢሊየን ዶላር ጠቅላላ ሃብት በማስመዝገብ የአራተኝነት ደረጃን እንደያዘ ነው።
ቤዞስ የ1 ቢሊየን፤ ቢል ጌትስ ደግሞ የ696 ሚሊየን ዶላር የሃብት መጠን ቅናሽ እንዳጋጠማቸው ተነግሯል።
አሜሪካውያኖቹ ሌሪ ኤሊሰን፣ ስቲቭ ባልሜር፣ ዋረን ቡፌት፣ ሌሪ ፔጅ፣ ሰርጌ ብሪን እና ማርክ ዙከርበርግ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።