የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ከግብፅ ፕሬዚዳንት ጋር በካይሮ ተወያዩ
በግድቡ ላይ ኢትዮጵያ አልቀበልም ያለችውን ሰነድ ያዘጋጁት ኃላፊው ዛሬ ካርቱም እንደሚገቡ ይጠበቃል
የግምጃ ቤት ኃላፊው ስቴቨን ምኑቺን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከአል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል
በግብፅና ሱዳን ጉብኝት ለማድረግ ወደ አፍሪካ የገቡት የአሜሪካው የግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ምኑቺን ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ መወያየታቸውን አህራም ዘግቧል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየሰራችው ባለው የሕዳሴ ግድብ ሰሞንኛ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ በካይሮ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ምኑቺን በግብፅና በሱዳን ቆይታቸው በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ባላግባቡ ጉዳዮች ዙሪያ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚጥሩ ገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም በግድቡ ላይ ግብጽ የምትፈልገው አስገዳጅ ስምምነት ላይ መግባባት እንዲኖር ለመስራት ወደ አፍሪካ መምጣታቸውን ኤምባሲውን ተቅሶ የግብፁ አህራም ጽፏል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት በሚለው ሀሳብ እንደማትስማማ መግለጿ ይታወሳል፡፡ ስቴቨን ምኑቺን የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአሜሪካ ሲደረግ ፣ ከታዛቢነት ሚናቸው አልፈው ፣ ድርድሩን በሦስተኛ ወገንነት ሲመሩ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በአሜሪካ ግምጃ ቤተ የተዘጋጀውን ሰነድም ኢትዮጵያ እና ሱዳን አንፈርምም ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስቴቨን ምኑቺን ዛሬ ካርቱም ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሱዳን ቆይታቸውም በግብፅ እንዳደረጉት ሁሉ ስለ ሕዳሴ ግድብ ድርድርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡