በኢራቅ በሚገኘው አሜሪካ መራሹ ጦር ላይ የሮኬት ጥቃት ተፈጽሞ አንድ ሰው ተገደለ
በኢራን የሚደገፉ የኢራቅ እና የየመን ታጣቂዎች በአሜሪካ እና በአረብ አጋሮቿ ላይ በቅርቡ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል
ጥቃቱን በኢራን የሚደገፍ ቡድን መፈጸሙ ተገልጿል
በሰሜን ኢራቅ የኤርቢል አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል የአየር ሰፈር ላይ ሰኞ ምሽት በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት የአንድ ሲቪል ኮንትራክተር ህይወት ሲያልፍ በጥምር ጦሩ የሚያገለግሉ አሜሪካውያን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በትንሹ ሶስት ሮኬቶች አውሮፕላን ማረፊያው ላይ እንደተተኮሱ እና ከነዚህም አንዱ የጥምር ኃይሉ ወታደሮች የሚገኙበትን መኖሪያ መምታቱን የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በጥቃቱ ህይወቱ ያለፈው ሲቪል ኮንትራክተር አሜሪካዊ አለመሆኑን የአሜሪካ ባለስልጣናት ያስታወቁ ሲሆን ሌሎች አምስት ኮንትራክተሮችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ጥምር ኃይሉ ገልጿል፡፡
ብዙም እውቅና የሌለው ቡድን ነው ጥቃቱን ፈጽሚያለሁ ያለው፡፡ ቡድኑ ከኢራን ጋር ግንኙነት እንዳለው አንዳንድ የኢራቅ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡ ዋሺንግተን እና ቴህራን ወደ ኑክሌር ስምምነቱ ሊመለሱ እንደሚችሉ በሚገመትበት ወቅት ነው ከኢራን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገመት ቡድን ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጥቃቱ ሀገራቸውን ማስቆጣቱን እና ስለ ጥቃቱ የሚደረገውን ምርመራ አሜሪካ እንደምታግዝ ገልጸዋል፡፡
በኢራን የሚደገፉ የኢራቅ እና የየመን ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ እና በአረብ አጋሮቿ ላይ በቅርብ ሳምንታት ጥቃቶችን የፈጸሙ ሲሆን ከነዚህም ጥቃቶች መካከል በሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት እና በባግዳድ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ የተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ይገኙበታል፡፡
ምንም እንኳን ባይደን ፕሬዝዳንት በሆኑ በቀናት ልዩነቶች የተፈጸሙት ጥቃቶቹ ብዙም ጉዳት ባያደርሱም ፣ በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች እና አጋሮቿ ላይ ጫና ፈጥረዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ፣ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተሰርዞ የነበረው የኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዲመለስ ውይይት ለመጀመር ማቀዱ እየተነገረ ነው፡፡ ይሁንና እንደ ፈረንሳይ ያሉ የአሜሪካ አጋሮች በውይይቱ ላይ ፣በመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛዋ የኢራን ባለአንጣ የሆነችው ፣ ሳዑዲ አረቢያም መሳተፍ እንዳለባት እየገለጹ ነው፡፡
ኢራን ወደ 2015ቱ ስምምነት የምትመለሰው አሜሪካ የጣለችባትን ማዕቀወቦች ካነሳች ብቻ መሆኑን አስታውቃለች ሮይተርስ እንደዘገበው፡፡