የትራምፕ ግብጽ “ግድቡን ታፈነዳዋለች” አስተያየት ቁጣን አስከትሏል
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በትዊተር ገጻቸው የትራምፕ “ንግግር ኃላፊነት የጎደለው ነው” ብለዋል
የትራምፕን አስተያየት ተከትሎ ኢትየጵያ ባወጣችው መግለጫ ግድቡን ከማጠናቀቅ የሚያግዳት ሃይል አለመኖሩን አስታውቃለች
የትራምፕን አስተያየት ተከትሎ ኢትየጵያ ባወጣችው መግለጫ ግድቡን ከማጠናቀቅ የሚያግዳት ሃይል አለመኖሩን አስታውቃለች
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ተገንብቶ ከመጠናቀቅ የሚያግደው ኃይል አለመኖሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በመግለጫው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ያለው የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሱዳንና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ወቅት ኢትዮጵያ የግድቡን ስምምነት ጥሳለች፤ ለግብጽ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አስቸጋሪ ስለሆነ “ግድቡን ያፈነዱታል” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
“የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው።” ብሏል መግለጫው፡፡
“በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ አንቀርም” ያለው መግለጫው ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም። አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው።” በማለት ያብራራል፡፡
መግለጫው ኢትዮጵያውያን ለወዳጆቻቸው እንጂ ለጠላት ተንበርክከው እንደማያውቁም የጠቀሰው መግለጫው ስለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር ያለው ነገር የለም፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በትዊተር ገጻቸው የፕሬዘዳንቱ “ንግግር ኃላፊነት የጎደለው ነው፤ ሰውየው ስለሚያወራው ነገር ምንም ፍንጭ የለውም” ብለዋል ጽፈዋል፡፡
“ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በእንደዚህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ፈርተው አያውቁም፤ ታሪክ ሁሉንም ያስተምራል” ብለዋል፡፡
ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን በትራምፕ ንግግር ንዴታቸውን በማህበራዊ ሚዲያ እየገለጹ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መጠናቀቂያ ላይ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት አከናውናለች፤ በሙሌቱም 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ ውኃ ለመሙላት ሳምንት እስከሚቀራት ድረስ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ውሃ ለመሙላት በተናጥል የምታደርገው እንቅስቃሴን እንደማይቀበሉት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡