አሜሪካ፤ “የምያንማር ጦር በሮሂንጊያ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል” አለች
የአሜሪካ ውሳኔ የሚያንማርን ጁንታ ተጠያቂ ለማድረግ ትልቅ ጫና የሚፈጥር ነው ተብሏል
ውሳሜው “ጁንታው ተጨማሪ በደል እንዲፈጽም የሚያደርግ ነው” የሚሉ ስጋቶች እየተንጸባረቁ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር “የምያንማር ጦር በሮሂንጊያ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል” ሲል አስታወቀ።
ሮይተርስ ከአሜሪካ ባለስልጠናት ነግረውኛል በሚል ይዞት የወጣ ዘገባ፤ የምያንማር ጦር አናሳ በሆኑት ሮሂንጋያ ሙስሊሞች ላይ የፈፀመው ድርጊት የዘር ማጥፋት እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን የአሜሪካ መንግስት መወሰኑን አስታውቋ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ መንግስታቸው የደረሰበትን ውሳኔ ባዛሬው ዕለት ዋሽንግተን በሚገኘውና “በአሁኑ ወቅት የሮሂንጊያዎችን ችግር በሚያሳየው የአሜሪካው ሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም” ተገኝተው እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል።
የምያንማር ጦር በፈረንጆቹ 2017 የመፈንቅለ መንግስት ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረበት አንስቶ በትረ ስልጣኑ አስካደላደለበት 2021 ድረስ በነበሩ ዓመታት፤ 730 ሺህ የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ወደ ባንግላድሽ መሰደዳቸው፣ በርካቶች በጀምላ እንደተቃጠሉ እና እንደተደፈሩ ሲዘገብ እንደበረ ይታወሳል።
በወቅቱ የአሜሪካ ባለስልጣናትና ሌሎች የውጭ ሀገራት የህግ ተቋማት የጭካኔውን ከባድነት በመገንዘብና መረጃዎች በመሰብሰብ ድርጊቱን በፍጥነት ለማጋለጥ ጥረት ቢያደረጉም ፤ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጉዳን በይደር በማስቀመጣቸው ውሳኔ ሳይሰጥበት ቆይቷል።
ፖምፒንዮን በመተካት ወደ ስልጣን የመጡት ብሊንከን በምያንማር ጉዳይ "ህጋዊ እና እውነት ላይ የተመረኮዘ ትንተና" እንዲደረግ በማዘዝ፤ የምያንማር ጁንታን ተጠያቂው ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲያከናውኑ ቆይተው አሁን ላይ የባይደን አስተዳደር ውሳኔ እስከማሳለፍ ደርሷል።
የአሜሪካ ውሳኔ የበርካታ የሰብዓዊ ተሟጋች ተቋማት ድጋፍ እንደሚኖረውም ከወዲሁ ተገምቷል፤ በተቃራኒው የአሜሪካ ውሳኔ ሌላ ስጋት የጫረባቸው አካላት አሉ።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣን፤ የባይደን አስተዳደር ውሳኔ ችግሩን ከማቃለል ይልቅ የምያንማር ጁንታ ተጨማሪ በደል እንዲፈጽም የሚያደርግ ነው” ሲሉ መደመጣቸውንም ነው ሮይተርስ የዘገበው።
በዋሽንግተን የሚገኘው የሚያንማር ኤምባሲም ሆነ የጁንታው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር እንደሌለም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት በሮሂንጊያዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ ሲከሰስ የቆየው ወታደራዊ ጁንታ፤ የኔ ዘመቻ በአሸባሪዎች ላይ ያነጣጠረ እንጂ በበሮሂንጊያዎች ላይ ያነጣጠረ አልነበርም እናም ከወንጀሉ ንጹህ ነኝ ሲል እንደነበር የሚታወስ ነው።