ህብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማይናማር፣ሩሲያ እና በሌሎችም ሃገራት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር አስታውቋል
የአውሮፓ ህብረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቤልጂዬም ብራሰልስ ተሰባስበዋል፡፡
ስብሰባው ለቀጣዮቹ 2 ቀናት የሚቀጥል ሲሆን በዋናነት ህብረቱ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ለመጣል ባሰባቸው ማዕቀቦች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የሩሲያ ዜጎችን ጨምሮ በአንዳንድ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ሊጣል የታሰበውን ማዕቀብ ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ‘ራፕትሊ’ የተሰኘውና መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ያደረገው የሩሲያ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው፡፡
ስብሰባው ኢትዮጵያን ጨምሮ ማይናማር፣ ቱርክ እና ቬንዙዌላን በመሳሰሉ ሀገራት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም የህብረቱ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
የህብረቱ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ናቸው ስብሰባውን የሚመሩት፡፡
ቦሬል ወደ ስብሰባው ሲገቡ በስፍራው ተገኝተው ለነበሩ ሚዲያዎች በሰጡት አጭር መግለጫ የፖለቲካ ትኩሳቱ “ከመብረድ ይልቅ እየጋለ” የመጣባቸው ሁለት ሃገራት አሉ ብለዋል፤ የምያንማር እና የኢትዮጵያን ስም በመጥቀስ፡፡
በሃገራቱ ያለው ሁኔታ “ከመሻሻል ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነው”ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ስብሰባው ተቀዳሚ አጀንዳው አደርጎ በጉዳዩ ላይ እንደሚመክር ተናግረዋል፡፡
ከምያንማር ጋር በተያያዘ ህብረቱ በመንግስት ግልበጣው እና በሰልፈኞች ጭቆና ላይ እጃቸው እንዳለበት በተጠረጠሩ 11 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀቱንም ነው ቦሬል የገለጹት፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ጋር የበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ዘግይተው የወጡ መረጃዎች ህብረቱ በቻይና ላይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ማዕቀብ መጣሉን ጠቁመዋል፡፡
ይህ የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የህብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት ነው መካሄድ የጀመረው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እና የሩሲያ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር የሚጠበቀው የህብረቱ ጠቅላላ ጉባዔ የፊታችን አርብ እንደሚጀመር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡