ብሪታኒያ እና አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያሉ ዜጎቻቸው ሀገሪቷን ለቀው እንዲወጡ አሳሳቡ
ሀገራቱ ዜጎቻቸው ሁሉንም የበረራ አማራጮች በመጠቀም ከአፋጋን እንዲወጡ አሳስበዋል
ሀገራቱ በአፍጋኒስታን ያለው የጸጥታ ሁኔታ “እጅግ” አሳሳቢ ስለሆነ ዜጎቻቸው ከአፍጋን እንዲወጡም ጠይቀዋል
አሜሪካ እና ብሪታኒያ፤ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ዜጎቻቸው ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ በአፍጋኒስታን ያለው የጸጥታ ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ነው ዋሸንግተን እና ለንደን በሀገሪቷ ያሉ ዜጎቻቸው እንዲወጡ ያሳሰቡት፡፡የብሪታኒያ የውጭ፣ የኮመን ዌልዝ እና ልማት ቢሮ በአፍጋኒስታን ያሉ ዜጎቹን ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ትናንትና ባወጣው መረጃ መግለጹን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
ሁሉም የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች አሁኑኑ አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣት አለባቸው ሲል ቢሮው አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱም ያለው የጸጥታ ሁኔታ “እጅግ” እንደሚያሳስበው የገለጸው የብሪታኒያው ተቋም ዜጎቹ በፍጥነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ከብሪታኒያ በተጨማሪም አሜሪካም ዜጎቿ ከአፍጋኒስታን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቷን አስታውቃለች፡፡ በአፍጋኒስታን የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በየትኛውም የበረራ አማራጭ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡ ኤምባሲው በአፍጋኒስታን አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በሀገሪቱ ለሚገኙ አሜሪካውያን የሚሰጠው ድጋፍ ውስን መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በካቡል የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከአፍጋኒስታን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለመሄድ የሚያስችል ገንዘብ ለሌላቸው አሜሪካውያን የመመለሻ ብድር እንደሚሰጥም ይፋ አድርጓል፡፡
ብሪታኒያ እና አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ዜጎቻቸው ያገኙትን የመጓጓዣ አማራጭ በመጠቀም በአስቸኳይ ከሀገሪቱ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአፍጋኒስታን የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣቱን ተከትሎ ታሊባን የሀገሪቱን በርካታ ቦታዎች እየተቆጣጠረ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ አሜሪካ ምንም እንኳን የአፍጋኒስታንን መንግስት እንደምትደግፍ ብትገልጽም ታሊባን ግን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እያሉ ሰላም እንደማይፈጠር መግለጹ ይታወሳል፡፡