ባይደን ዩክሬን ከአሜሪካ በተላኩላት ሚሳኤሎች ሩሲያን እንድትመታ ፈቀዱ
ዋሽንግተን እስከ 300 ኪሎሜትር የሚጓዙት ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ መዋል ከሞስኮ ጋር በቀጥታ ያጋጨኛል በሚል ስታመነታ ቆይታለች
ፕሬዝዳንት ፑቲን የአሜሪካ ሚሳኤሎች በሩሲያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም ከዋሉ የኒዩክሌር ጦርነት ሊያስነሳ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን ከአሜሪካ በተላኩላት ሚሳኤሎች በሩሲያ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ፈቀዱ።
ባይደን ኬቭ ለወራት ስታነሳው የነበረውን ከድንበሯ ውጭ (በሩሲያ መሬት ውስጥ) የአሜሪካን ሚሳኤሎች የመጠቀም ጥያቄ የተቀበሉት በጥር ወር ዋይትሃውስን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ “እንዲህ አይነት ጉዳዮች በይፋ አይገለጹም፤ ሚሳኤሎቹ ራሳቸው ይናገራሉ” በማለት ከዋሽንግተን ፈቃድ ማግኘታቸውን በተዘዋዋሪ አረጋግጠዋል።
የባይደን አስተዳደር ከሞስኮ በሚነሱ ቅሬታዎች እና ማሳሰቢያዎች ምክንያት አሜሪካ ለዩክሬን የላከቻቸው ረጅም ርቀት ሚሳኤሎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ለማድረስ እንዳይውሉ ሳይፈቅድ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ምዕራባውያን ሀገራት መሰል ውሳኔ ካሳለፉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት(ኔቶ) በዩክሬኑ ጦርነት “በቀጥታ እንደተሳተፈ ይቆጠራል”፤ የኒዩክሌር ጦርነትም ሊያስነሳ ይችላል በሚል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።
አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው ዋሽንግተን ይህንኑ በመፍራት ይመስላል የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቿ ጥቅም እንዲውሉ የፈቀደችው ዩክሬን በነሃሴ ወር የሩሲያን ድንበር ጥሳ በገባችበት ኩርስክ ክልል ነው።
አሜሪካ እስከ 300 ኪሎሜትር ድረስ የሚጓዙት ሚሳኤሎች ሩሲያን ለማጥቃት እንዲውሉ የፈቀደችው ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬኑ ጦርነት እንዲሳተፉ መፍቀዷን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በነሃሴ ወር ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል የገቡትን የዩክሬን ወታደሮች ለማስወጣት በቅርብ ቀናት ውስጥ መጠነሰፊ ውጊያ እንደሚጀምሩ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ዩክሬን በኩርስክ ክልል ከ11 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እንደሚገኙ ማስታወቋ ይታወሳል።
የፕሬዝዳንት ባይደን ውሳኔ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ለኬቭ የላኩት “ስቶርም ሻዶው” የተሰኘው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ለማድረስ እንዲውል ፈቃድ መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
ይሁን እንጂ ለንደንም ሆነች ፓሪስ ለባይደን ውሳኔ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም።
የጀርመኑ የጥናት ተቋም ኬል ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው አሜሪካ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለኬቭ ከ55 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጋለች።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ዋይትሃውስ ሲዘልቁ ከሚከውኗቸው ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል የዩክሬኑን ጦርነት ማስቆም እንደሆነ መግለጻቸው አይዘነጋም።