ዩክሬን አሜሪካ በሚስጢር በላከችላት ባለስቲክ ሚሳኤሎች ሩሲያን ማጥቃት መጀመሯ ተነገረ
አሜሪካ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ መሬት ዘልቀው ይገባሉ በሚል ለኬቭ ላለመላክ ስታመነታ ቆይታለች
ሩሲያ የአሜሪካና አጋሮቿ ወታደራዊ ድጋፍ አስከፊ የኒዩክሌር ጦርነት ያስነሳል በሚል እያስጠነቀቀች ነው
አሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ዩክሬን መላኳ ተነገረ።
ኬቭ 300 ኪሎሜትር የሚምዘገዘገውን ሚሳኤል በክሬሚያ የሚገኝ የሩሲያ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ለመምታት ተጠቅማበታለች ተብሏል።
አዳዲሶቹ ሚሳኤሎች በበርድያንስክ ከተማ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዋላቸውንም ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
ዋሽንግተን ምን ያህል ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ኬቭ መላኳን ይፋ ባታደርግም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሚሳኤሎቹ እንዲላኩ ፈቃድ ሰጥተዋል ነው የተባለው።
መጠናቸው ያልተጠቀሰ ተጨማሪ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ለመላክ መታቀዱንም የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ ተናግረዋል።
በዚህ ወር ኬቭ ደርሰዋል የተባሉት ሚሳኤሎች ፕሬዝዳንት ባይደን በመጋቢት ወር ባጸደቁት የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የተካተቱ ስለመሆናቸውም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ለዩክሬን አጭር ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎችን የላከችው ዋሽንግተን ወደ ሩሲያ ይዞታ ዘልቀው መግባት የሚችሉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን መላክ ከሞስኮ ጋር በቀጥታ ያጋጨኛል በሚል ስታመነታ ቆይታለች።
ኬቭ በበኩሏ ሚሳኤሎቹ የተጓተተውን የመልሶ ማጥቃት ዳግም ለመጀመር እንደሚያግዙ ገልጻለች።
በተያያዘ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የህግ መወሰኛ ምክርቤቱ አጽድቆ የላከላቸውን ለዩክሬን የሚደረግ የ61 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ ማዕቀፍ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ “አሁን ለአንድ አመት ከግማሽ በጥርጣሬና ክርክር ያሳለፍነው ጊዜ አክትሞ ያሻንን ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።
በተተኳሽ እና የአየር መቃወሚያ እጥረት የምዕራባውያኑን እጅ ሲጠብቁ የከረሙት ዜለንስኪ፥ የአሜሪካ ድጋፍ የጦርነቱን አውድ በፍጥነት እንደሚቀይረው አምነዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍ ኬቭን ይበልጥ ያፈራርሳት እንደሆነ እንጂ የሚለውጠው ነገር የለም ብላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ በቅርቡ “ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ድጋፍ አሜሪካና አጋሮቿ ከሞስኮ ጋር በቀጥታ ለማጋጨት ተቃርቧል” ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንም በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች አንስቶ የኒዩክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።