"ሩሲያ በዩክሬን በከፈተችው ጦርነት መቀጣት አለባት" - አሜሪካ
ዋሽንግተን የሩሲያ ዝም መባል ለሌሎች ለአጥቂዎች መልዕክት ይሆናል በሚል ስጋቷን አስቀምጣለች
ቡድን 20 በሩሲያ-ዩክሬይን ጦርነቱ ላይ የጋራ መግለጫ ለመስጠት መስማማት አልቻለም
አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት መቀጣት አለባት ስትል አስታወቀች።
ይህን ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከህንድ፣ ጃፓን እና አውስትራሊያ ጋር በኒው ዴልሂ ከተገናኙ በኋላ ነው።
ኳድ እየተባለ የሚጠራው የሀገራቱ ቡድን ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ ሩሲያ በዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀም "ተቀባይነት የለውም" ብሏል።
- ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷን አስታወቀች
- የአሜሪካና ጀርመን መሪዎች ወደ “ኒውክሌር ጦርነት” እንዳንገባ ኃላፊነታቸውን ይወጡ - ሜድቬዴቭ
ከሳምንታት በፊት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ታሪካዊ" የተባለውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስምምነት መሰረዛቸው የሚታወስ ነው።
ፑቲን የኒውክሌር ሙከራዎችን እንደሚቀጥሉም ዝተዋል።
ብሊንከን በህንድ በተካሄደውና የኳድ ሚንስትሮችም በተገኙበት የቡድን 20 ስብሰባ ላይ "ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ እየሰራች ያለችውን እንድትፈጽም ከፈቀድንላት፤ ይህ በሁሉ ቦታ ለአጥቂዎች መልዕክት ነው" ብለዋል።
ከኒው ዴሊ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ብሊንከን የዩክሬን ግጭት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተገናኝተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ብሊንከን በውይይቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞስኮ ጦርነቱን እንድታቆም እና የኒውክሌር ስምምነቱን መልሳ እንድታጸድቅ አሳስብዋል ሲሉ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናግረዋል።
በቡድን 20 ስብሰባ አሜሪካ እና አጋሮቿ ለአባል ሀገራት፤ ሩሲያ ግጭቱን እንድታቆም ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ነገር ግን ሩሲያ በመቃወሟ የተነሳ በጦርነቱ ላይ ቡድኑ የጋራ መግለጫ ለመስጠት መስማማት አልቻለም ተብሏል።