ባይደን፤ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ በፊርማቸው አጸደቁ
ባይደን የአሜሪካ ኮንግረስ ከወር በፊት አሳልፎት የነበረውን የውሳኔ ሃሳብ ነው ያጸደቁት
የሀገራቱን ጥያቄ የደገፉ የኔቶ አባል ሃገራት ቁጥር 23 ደርሷል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ በፊርማቸው አጸደቁ፡፡
ባይደን የአሜሪካ ኮንግረስ ከወር በፊት አሳልፎት የነበረውን የውሳኔ ሃሳብ ነው ያጸደቁት፡፡
የሁለቱ የኖርዲክ ሃገራት ኔቶን መቀላቀል ጥምረቱን የበለጠ እንደሚያጠናክረው ነው ባይደን የተናገሩት፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጠንካራ የዲሞክራሲ፣ ወታደራዊ ተቋማት ባለቤት ናቸው ያሏቸውን ፊንላንድን እና ስዊድንን ግልጽና ጠንካራ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባትም ችለዋል በሚል አሞግሰዋቸዋል፡፡
የ76 ዓመቱ አዛውንት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ስለመላላቱ የሚነገርለትን የአሜሪካንና የአጋሮቿን ግንኙነት መልሶ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ቃል በመግባት ነበር ወደ ስልጣን የመጡት፡፡
የአሜሪካ ደህንነት መሰረት ነው ሲሉም ኔቶን አሞካሽተዋል፡፡ ሃገራቸው በአትላንቲክ ቀጣና ለሚኖራት ጥምረት ያላትን ቁርጠኝነትንም ገልጸዋል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር (ኔቶ) አባል ለመሆን የሚጠይቁ አዳዲስ ሃገራት የጥምረቱን አባል ሃገራት ሙሉ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ የኪቭ እጣ ፋንታ ሊገጥመን ይችላል በሚል ኔቶን ለመቀላቀል የጠየቁት ፊንላንድ እና ስዊድንም ከ30ዎቹ የጥምረቱ አባል ሃገራት የ23ቱን የተረጋገጠ ድጋፍ ማግኘታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የኔቶን በአትላንቲክ ቀጣና መስፋፋት አጥብቃ ስትቃወም የነበረችው ሩሲያ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን መቀላቀላቸው ያን ያህል ስጋት እንዳይደለ ብትገልጽም ከበድ ያለ የአጸፋ ምላሽን ልትሰጥ እንደምትችል ግን ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡