አሜሪካ፤ “የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሃት ጸብ አጫሪ ከሆነ ድርጊት” እንዲቆጠቡ አሳሰበች
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መልዕከተኛ ዓባይ ለልማት ያለውን ጥቅም መረዳታቸውን ገልጸዋል
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አሜሪካ ጉባዔ ላይ እንዲትሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል
አሜሪካ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሃት ጸብ አጫሪና ጥላቻን ሰባኪ ከሆኑ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳሰበች።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ፤ በመቀሌ እና በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ አውጥቷል። ዋሸንግተን፤ መንግስትና ህወሃት ንግግር እንዲጀምሩ እንደምታበረታታ ማስታወቋን ኤምባሲው አስታውቋል።
- የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ድርድር ተስፋ እና ስጋቶች
- መንግሰት፤ ህወሓት የሰላም ሂደቱ ላይ መሰናክል እየፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳርፍበት ጠየቀ
አሜሪካ፤ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ድርድር እንደምትደግፍና እንደምታበረታታ የገለጸች ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ግን ጸብ አጫሪ ከሆኑ ድርጊቶች ሊቆጠቡ ይገባል ማለቷን ኤምባሲው ገልጿል።
ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር የሰላም ንግግር በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከአፍሪካ ሕብረት ተወካዮችጋር መነጋገራቸው በመግለጫው ተካቷል።
በአውሮፓውያኑ 2021 አሜሪካ ለጤና፣ ለልማትና ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል አንድ ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ወይም 68 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ድጋፍ ማድረጓንም ኤምባሲው ይፋ አድርጓል።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታን መጎብኘታቸውና ይህም መሻሻል እያሳዬ መሆኑ ተገልጿል። በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ነዳጅ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መድረሱም ተገልጿል።
አሜሪካ፤ በኢትዮጵያ ላለው ድርቅ ምላሽ የሚሆን 488 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ኤምባሲውአስታውሷል። አሜሪካ፤ በዚህ ፈታኝ በሆነ ወቅት ከኢትዮጵያውያን ጎን እንደሆነችም ገልጻለች።
በአፍሪካ ቀንድ አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
አምባሳደር ማይክ ሃመር ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተወካዮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ በፈረንጆቹ ከታህሳስ 13 እስከ 15 በሚካሄደው የአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ እንዲትሳተፍ ግብዣ እንዲላክ በአፅንኦት አያሣሰቡ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል።
ተወካይ አምባሳደሯ የኢትዮጵያ በጉባዔው መሳተፍ ለሁለቱ ሀገራት እንዲሁም ለአሜሪካ አሜሪካ ግንኙነት የላቀ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስለዓባይ ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ብዙ መረዳታቸውን መግለጻቸውንም ኤምባሲው አስታውቋል።