አሜሪካ ለዩክሬን አንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው አዲስ የጦር መሳሪያ ልታስጣጥቅ እንደሆነ ተገለጸ
የአሁኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ሁሉ ከፍተኛው ነው
የጦር መሳሪያውን ሩሲያ እንዳታወድመው በከፍተኛ ጥንቃቄ ወደ ዩክሬን ይጓጓዛል ተብሏል
አሜሪካ ለዩክሬን አንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው አዲስ የጦር መሳሪያ ልታስጣጥቅ እንደሆነ ተገለጸ።
ከተጀመረ 165 ቀኑ ላይ የሚገኘው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እስካሁን መቋጫ አላገኘም።
ጦርነቱን በአሜሪካ አስተባባሪነት ምዕራባዊያን እና ሌሎች ሀገራት በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
አሜሪካ በሩሲያ ላይ በተናጥል እና በቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
አሁን ደግሞ አንድ ቢሊዮን ዶናር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን ልታስታጥቅ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሁኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ሁሉ ከፍተኛው ነው ተብሏል ።
በአጠቃላይ ሩሲያ እና ዩክሬን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ ለዩክሬን የለገሰቻቸው የጦር መሳሪያ 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል።
በአሁኑ የጦር መሳሪያ ልገሳ ፓኬጅ መሰረት ለዩክሬን ከሚሰጡ የጦር መሳሪያዎች መካከል ሂማርስ፣ ናስማስ፣ ኤም113 እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ዩክሬን ከሩሲያ ለሚሰነዘሩባት የየብስ፣ባህር እና አየር ላይ ጥቃቶችን ለመመከት ያስችላታል ተብሏል።
ይህ አዲሱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ነገ እንደሚፈረም የሚጠበቅ ሲሆን፤ በጥንቃቄ ወደ ዩክሬን ይጓጓዛል ተብሏል ።
ሩሲያ በበኩሏ ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ማስታጠቃቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ባለፉት ጊዜያት ውስጥም አሜሪካንን ጨምሮ ከምዕራባዊያን ለዩክሬን የተለገሱ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን አውድሜያለሁ ማለቷም አይዘነጋም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በየዕለቱ እስከ 200 ወታደሮች በሩሲያ ጥቃት እየተገደሉባቸው እንደሆነ ገልጸው ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እንዲለግሱም ጥሪ አስተላልፈው ነበር።