ባይደን ለሊዮኔል ሜሲ የነጻነት የክብር ሽልማት ሰጡ
አርጀንቲናዊው ኮከብ የክብር ሽልማቱ ከተሰጣቸው 19 ሰዎች መካከል ቢካተትም ሽልማቱን በዋይትሃውስ አልተቀበለም
ሜሲ የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን በጤና እና ትምህርት ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ለሽልማት አብቅቶታል
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሜሲ የነጻነት የክብር ሽልማት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ትልቅ ክብር የሚሰጠውን ሽልማት ለ19 ሰዎች ማበርከታቸውን ዋይትሃውስ አስታውቋል።
የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ኪሊንተን፣ ተዋናዩ ዴንዝል ዋሽንግተን፣ ድምጻዊው ቦኖ እና ማጂክ ጆንሰን ሽልማቱን ከባይደን ተቀብለዋል።
አርጀንቲናዊው የእርኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ግን በዋይትሃውስ በተካሄደው የሽልማት ስነስርአት ላይ አልተገኘም።
"ሜሲ ሽልማቱ ስለተሰጠው ትልቅ ክብር አለው፤ አስቀድሞ ከተያዘ ቀጠሮ እና ሌሎች ሃላፊነቶች ጋር በተያያዘ ግን ሽልማቱን በአካል ተገኝቶ መቀበል አልቻለም" ብለዋል የሜሲ የማኔጅመት ቡድን እና ክለቡ ኢንተርሚያሚ በጋራ ባወጡት መግለጫ።
ዩኤስኤ ቱዴይ ሜሲ በቅርቡ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር በመገናኘት ሽልማቱን እንደሚቀበል ዘግቧል።
ሊዮኔል ሜሲ የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ የበጎፈቃድ አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል።
ተጫዋቹ በመላው አለም በትምህርት እና ጤና ዘርፍ የሚካሄዱ ስራዎችን በመደገፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ባይደን ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የነጻነት የክብር ሽልማት እንዲሰጡት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።
ሜሲ "እያንዳንዱ ህጻን ምኞቱን እውን ለማድረግ ተመሳሳይ እድል ማግኘት አለበት" በሚል በ2007 የ"ሊዮኔል ሜሲ ፋውንዴሽን"ን በማቋቋም በተለይ ግጭት ባለባቸው ሀገራት ለሚገኙ ህጻናት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
የ37 አመቱ አርጀንቲናዊ በተጫወተባቸው ክለቦች 45 ዋንጫዎችን በማንሳት ደማቅ ታሪክ አጽፏል።
ከፒኤስጂ ወደ አሜሪካው ኢንተርሚያሚ ካቀና በኋላ የእግርኳስ ዘመኑ እያከተመ ነው ቢባልም ክለቡን በ2023 ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋንጫ ጋር ማገናኘቱ ይታወሳል።
በዚህ የውድድር አመትም 20 ጎሎችን አስቆጥሮ 16 ጎል የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።
የሮዛሪዮው ተወላጅ በእያንዳንዱ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ሁሉ በሚባል ደረጃ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በእግርኳስ ህይወቱ ማሳካት የሚፈልገውን የአለም ዋንጫም በ2022 ሀገሩን ከ1986 በኋላ ለዋንጫ በማብቃት እውን ማድረጉ አይዘነጋም።