ከሮናልዶ እና ሜሲ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ስኬታማው ማን ነው?
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ከ10 አመት በፊት በተደረገው የአቴንስ ኦሎምፒክ በ19 አመቱ ለሀገሩ ተጫውቷል
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በበኩሉ በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ ተሳትፎ የወርቅ ሜዳልያ ማጥለቁ ይታወሳል
ፓሪስ ያዘጋጀችው አንጋፋውና ተጠባቂው የኦሎምፒክ ውድድር የፊታችን አርብ ይጀመራል።
አትሌቲክስን ጨምሮ 32 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት የፓሪስ ኦሎምፒክ የእግርኳስ ግጥሚያዎችንም ያስተናግዳል።
16 የወንድ፤ 12 የሴት የኣግርኳስ ብሄራዊ ቡድኖችም የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ለማጥለቅ ይፎካከራሉ።
የ21ኛው ክፍለዘመን የእግር ኳስ ፈርጥ የሚባሉት ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግን በፓሪስ አይገኙም፤ ሮናልዶ ሀገሩ ለውድድሩ ስላላለፈች፤ ሜሲ ደግሞ ሀገሩ ብታልፍም ከኮፓ አሜሪካው ተሳትፎ በኋላ ጫና እንዳይበዛብኝ በሚል አይሳተፉም።
በኦሎምፒክ ተሳትፎ ከሮናልዶ እና ሜሲ ማን የተሻለ ውጤት አለው?
ፖርቹጋላዊው ኮከብ በእግርኳስ ህይወቱ ያላሳካው ነገር ቢኖር የአለም ዋንጫ እና ኦሎምፒክ ነው።
በ2016 ከሀገሩ ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ያሳካው ሮናልዶ ከተለያዩ ክለቦች ጋር በርካታ ዋንጫዎችን ቢያነሳም በኦሎምፒክ ተሳትፎውም ሆነ ውጤቱ በስኬት የሚጠቀስ አይደለም።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኦሎምፒክ የእግርኳስ ጨዋታ የተሳተፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ከ20 አመት በፊት በአቴንስ በተካሄደው ኦሎምፒክ።
በወቅቱ 19 አመቱ ላይ የነበረው ሮናልዶ ከኢራቅ፣ ሞሮኮ እና ኮስታሪካ ጋር የተደለደለችውን ሀገሩን ለውጤት እንደሚያበቃ ቢጠበቅም ገና በመክፈቻው በኢራቅ 4 ለ 2 መሸነፋቸው ይታወሳል።
ሮናልዶ ሞሮኮን 2 ለ 1 ባሸነፉበት ጨዋታ ግብ ከማስቆጠሩ ውጭ ሀገሩን የምድቡ የመጨረሻ ሆና ከማጠናቀቅ መታደግ አለመቻሉንም መረጃዎች ያወሳሉ።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ከአቴንስ ኦሎምፒክ በኋላ በታሪካዊው መድረክ አልተሳተፈም።
በኦሎምፒክ የሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖች እድሜያቸው ከ23 አመት በላይ የሆኑ ሶስት ተጫዋቾችን ማካተት ቢችሉም ሮናልዶ ይህን እድል አግኝቶ በሌሎች የኦሎምፒክ ግጥሚያዎች ላይ ሀገሩን ወክሎ አልተገኘም።
በአንጻሩ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲ የአለም ዋንጫ በማንሳትና በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት ከሮናልዶ የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል።
ሜሲ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው ኦሎምፒክ ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ለዋንጫ አብቅቷል።
ተጫዋቹ ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ ሻምፒዮን ለሆነው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል፤ በምድብ ጨዋታ በኮቲዲቯር ላይ እና በሩብ ፍጻሜው በኔዘርላንድስ ላይ።
ሊዮኔል ሜሲ በአሜሪካ በተካሄደው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ከሀገሩ ጋር ዋንጫ ያነሳው ሜሲ በፓሪስ ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹን እንደማይቀላቀል አሳውቋል።