ሩሲያ ከለቀቀቻቸው እስረኞች መካከልም ለዩክሬን ሲዋጉ የተያዙ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያና የሞሮኮ ዜጎች ይገኛሉ
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ ከ7 ወራት ገደማ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገለጸ።
በጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ሀገራት 300 ገደማ እስረኞችን መለዋወጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ከለቀቀቻቸው የጦር እስረኞች መካከልም ለዩክሬን ሲዋጉ የተያዙ እና በቅጥረኛ ተዋጊነታው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያ እና የሞሮኮ ዜጎች ይገኙበታል።
በሩሲያ የተለቁት የውጭ ዜጎችም አምስት የብሪታኒያ፣ ሁለት የአሜሪካ፣ አንድ የሞሮኮ እና አንድ የሰውድን ዜጎች ሲሆኑ፤ ሳዑዲ አረቢያ መግባታውም ታውቋል።
በተጨማሪም ሩሲያ በማሪፑል ውጊያ ላይ በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን 215 ዩክሬናውያንን የለቀቀች ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ኮማንደሮች እንደሆኑም ተመላክቷል።
ዩክሬንም 55 ሩሲያውያንን እና ለሩሲያ ወግነው ሲዋጉ የነበሩ ዩክሬናውያንን የለቀቀች ሲሆን፤ ከእነዚህም የሩሲያ ደጋፊ የሆነ ፓርቲ መሪ የሆነው እና በሀገር ክህደት ወንጀል ተከሶ የነበረው ቪክቶር ሜድቭድቼክ ይገኝበታል።
የሩሲያ እና ዩክሬን የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት በሳዑዲ አረቢያ እና በቱርክ አመቻችነት መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን፤ ስምምነቱ ለተወሰነ ጊዜ በዝግጅት ሂደት የቆየ እና ከፍተኛ ጭቅጭቅ ፈጠረ ነበር።
ከዚህ ቀደምም በሳዑዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን አሸማጋይነት 10 የውጭ ዜጎች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስረኛ ልውውጡን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ፤ “ይህ ለሀገራችንም ይሁን ለህዝባችን ትልቅ እና ግልጽ ድል ነው፤ ዋናው ነገር 215 ዩክሬናውያን በሰላም ከሚወዷቸው ቤተሰቦቻው ጋር መቀላቀላቸው ነው” ብለዋል።
"ሁሉንም ህዝቦቻችንን እናስታውሳለን፤ እያንዳንዱን ዩክሬን ዜጋ ለማዳን እንሞክራለን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ይህ የዩክሬን ትርጉም ነው፣ የእኛ ማንነት፣ ከጠላት የሚለየን ይህ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።