ፕሬዝዳንት ሺ አምባገነን መሪ ናቸው - ባይደን
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በካሊፎርኒያ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ነው የቻይና አቻቸውን በአምባገነንነት የከሰሱት
አሜሪካ እና ቻይና ከቀናት በፊት የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማምተው ነበር
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቻይና አቻቸውን “አምባገነን” መሪ ናቸው አሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከን በቤጂንግ ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ምክክር ባደረጉ ማግስት የተሰማው አስተያየት ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ፕሬዝዳንት ሺ እና ብሊንከን የሀገራቱን የተካረረ ግንኙነት የሚያለዝቡ ውይይቶች እንዲደረጉ መስማማታቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ራሳቸው ባይደንም ሰኞ እለት የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ወደ ትክክለኛው መስመር እየተመለሰ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት ምሽት በካሊፎርኒያ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ግን ብሊንከን ሰኞ እለት “ቢዘጋ” ይሻላል ያሉትን አጀንዳ አንስተዋል።
ፕሬዝዳንት ሺ የቻይና እንደሆኑ የተጠረጠሩት ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛዎች በአሜሪካ የአየር ክልል ተመተው በመውደቃቸው ሀፍረት ተሰምቷቸዋል ነው ያሉት ባይደን።
“ሺ ጂንፒንግ በወቅቱ የተረበሸው በስለላ ቁሳቁሶች የተሞላው ተንሳፋፊ ፊኛን መትቼ ስጥለው የት እንዳለ እንኳን ስለማያውቅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ይህ ለአምባገነኖች እጅግ አሳፋሪ ነገር ነው፤ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ሳያውቁ ሲቀሩና ባልጠበቁት መንገድ ስንመታው (ፊኛውን) ተበሳጭተዋል” በማለትም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እስካሁን ለባይደን አስተያየት ምላሽ አልሰጡም።
ከአምስት አመት በኋላ ወደ ቻይና ከፍተኛ ባለስልጣኗን ልካ የነበረችው አሜሪካ፥ ውጥረቱ ረገበ ሲባል ዳግም ቁርሾ የሚቀሰቅስ ንግግር በፕሬዝዳንቷ በኩል ተሰምቷል።
ዋሽንግተን እና ቤጂንግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ከስምምነት ላይ ይድረሱ እንጂ አሁንም የልዩነት ምንጭ የሆኑ በርካታ ጉዳይ አላቸው።
የንግድ፣ የሰብአዊ መብት እና የታይዋን ጉዳይ ሃያላኑን ሀገራት እንዳፋጠጡ ናቸው።