ቤጂንግ የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው አለች
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዩ በተቀናቃኞቹ ኃይሎች መካከል አለመግባባትን ለመፍታት አንገብጋቢ በተባሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደረጃ ከአምስት ዓመታት በኋላ በቻይና የመጀመሪያውን ጉብኝት ያደረጉት ብሊንከን፤ በቤጂንግ ከዋንግ ጋር ለሦስት ሰዓታት ያህል መነጋገራቸውን ተነግሯል።
የቀድሞ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ዋንግ የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳለ ገልጸው፤ ዋናው መንስኤ አሜሪካ ለቻይና ያላት የተሳሳተ አመለካከት ነው ብለዋል።
"ለህዝብ፣ ለታሪክ እና ለዓለም ኃላፊነት የተሞላበት አመለካከት ልንይዝ እና የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነትን ከቁልቁለት መቀልበስ አለብን" ብለዋል።
ከአንድ ቀን በፊት ብሊንከን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ጋር ከ7 ሰዓታት ተኩል መነጋገራቸው ታውቋል።
ዋሽንግተን ሁለቱንም የውይይት መድረኮች "ቅን" እና "ገንቢ" በማለት ገልጻለች።
ብሊንከን ከቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ይገናኛሉ ወይ የሚለው ላይ አይን ተጥሏል።
ዋንግ አሜሪካ ቻይና ላይ የምታደርሰውን ስጋት እንድትገታ፣ የቻይናን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትን "ማፈን" እንድታቆም እና በውስጥ ጉዳዮቿ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ማሳሰባቸውን የቻይና መንግስት ሚዲያ ዘግቧል።
የታይዋንን ጉዳይ በተመለከተ ቤጂንግ "የግዛቴ አካል" ናት የምትላት ሲሆን፤ ዋንግ "ቻይና ለመደራደርም ሆነ ለመስማማት ቦታ የላትም" ብለዋል።