ኤምሬትስ የአሜሪካ ሁለተኛዋ ”ዋነኛ የመከላከያ አጋር” ሆነች
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋይትሃውስ ከአረብ ኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ጋር መክረዋል
አቡ ዳቢ እና ዋሽንግተን የጋራ ወታደራዊ ልምምድና ትብብር ለማድረግ ተስማምተዋል
ኤምሬትስ የአሜሪካ ሁለተኛዋ ”ዋነኛ የመከላከያ አጋር” ሆነች።
በአሜሪካ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዋይትሃውስ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር መክረዋል።
ዋይትሃውስ ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ መሪዎቹ የሀገራቱን ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውን አመላክቷል።
አሜሪካ የኤምሬትስን ደህንነት እና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የውጭ ስጋቶችን ለመከላከል የቴክኖሎጂና ሌሎች ድጋፎችን እንደምታደርግም ነው ዋይትሃውስ የገለጸው።
አሜሪካ እና ኤምሬትስ ግጭትን ለመከላከልና ለማብረድ የጋራ አቋም ይዘው የደህንነት ትብብራቸውን ማጠናከራቸውን በማንሳትም የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር አቡ ዳቢን ሁለተኛዋ “ዋነኛ የመከላከያ አጋር” አድርጎ እውቅና እንደሰጣት አብራርቷል።
የባይደን አስተዳደር በ2021 ህንድን “ዋነኛ የመከላከያ አጋር” አድርጎ መመዝገቡ የሚታወስ ነው።
ኤምሬትስም የአሜሪካ የመከላከያ አጋር መሆኗ ከዋሽንግተን ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግና የደህንነት ትብብሯን ይበልጥ ለማሳደግ ያግዛታል ተብሏል።
የ”ዋነኛ የመከላከያ አጋር” እውቅናው “በመካከለኛው ምስራቅ፣ ምስራቅ አፍሪካ እና ህንድ ውቅያኖስ ክልል ወታደራዊ ትብብርን ይበልጥ የሚያጎለብት ነው” ብሏል ዋይትሃውስ በመግለጫው።
ፕሬዝዳንት ባይደን እና ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እስራኤል በሊባኖስ ጥቃቷን አጠናክራ 500 የሚጠጉ ሰዎችን በአየር ድብደባ በገደለችበት እለት ነው የመከሩት።
መሪዎቹ በጋዛ እና ሊባኖስ እየተካሄዱ የሚገኙ ጦርነቶች አድማሳቸውን አስፍተው የመካከለኛው ምስራቅን ወደ ቀውስ ሳይከቱ እንዲቆሙና ለፍልስጤማውያን የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና ባይደን የ50 አመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ኤምሬትስ እና አሜሪካ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ህዋ ምርምር እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይም መምከራቸው ተገልጿል።