ቱርክ 500 የሚጠጉ ሊባኖሳውያን የተገደሉበትን ጥቃት አወገዘች
“የኔታንያሁን ደም በማፍሰስ ፖለቲካዊ ፍላጎት የማሳካት ጥረት” የሚያግዙ ሀገራት ድጋፋቸውን እንዲያቆሙም አሳስባለች
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን በኒውዮርክ ከኢራን፣ ጀርመን፣ ግሪክና ኩዌት መሪዎች ጋር መክረዋል
እስራኤል በሊባኖስ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት አጥብቃ እንደምትቃወም ቱርክ ገለጸች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የቴል አቪቭ ጥቃት “ቀጠናውን ወደ ቀውስ የመክተት አላማ ያለው ነው” ብሏል።
ለእስራኤል ያልተገደበ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ሀገራት “የኔታንያሁን ደም በማፍሰስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን የማሳካት ጥረት እያገዙ ነው” ያለው ሚኒስቴሩ፥ እንደ ተመድ ያሉ የአለም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተቋቋሙ ድርጅቶች በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።
የሊባኖስ መንግስት እስራኤል በትናንትናው እለት በፈጸመች የአየር ድብደባ 492 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ከአስርት አመታት በኋላ በአንድ ቀን የበርካታ ሊባኖሳውያን ህይወት የቀጠፈው ጥቃት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉም ነው የተገለጸው።
በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ኒውዮርክ የገቡት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የትናንቱን የእስራኤል የአየር ድብደባ ማውገዛቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ኤርዶሃን ከኢራን፣ ጀርመን፣ ግሪክና ኩዌት መሪዎች እንዲሁም ከአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካን ጋር ተወያይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅትም “የኔታንያሁ አስተዳደር አለማቀፉን ህግ እና ሰብአዊ መብቶችን ለመጣስ ምንም አያመነታም፤ ይህም የሚያስቆመኝ የትኛውም ሃይል የለም ከሚል ቅዠት የመነጨ ነው” ብለዋል።
በጋዛም ሆነ በሊባኖስ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ አለማቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ነው ኤርዶሃን ያሳሰቡት።
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በእስራኤል ላይ የጀመረውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ አጠናቆ ተገቢውን ቅጣት ታገኝ ዘንድም ለካሪም ካን ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ እስራኤል በጋዛ ለ11 ወራት ስትፈጽመውን የቆየችውን ድብደባ በተደጋጋሚ አውግዛለች።
አንካራ ከቴል አቪቭ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጣ በአለማቀፉ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ የቀረበውን ክስ ደግፋ ለመከራከር በይፋ መጠየቋም ይታወሳል።