ፕሬዝደንት ዢ በቡድን 20 ሀገራት ጉባዔ አይሳተፉም መባሉ እንዳበሳጫቸው ባይደን ተናገሩ
በኒው ደልሂ በሚደረገው ጉባኤ የቻይና እና ሩሲያ መሪዎች አይገኙም
በህንድ በሚካሄደው ስብሰባ የቻይናን የልኡካን ቡድን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ መሆናቸው ተገልጿል
የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጅንፒንግ በቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ እንዳማይሳተፉ መገለጹ እንዳበሳጫቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
"ተበሳጭቻለሁ፣ ላገኘው እፈልግ ነበር።" ያሉት ባይደን ስብሰባው መቼ እንደሚካሄድ ግን አልገለጹም።
ቤጅንግ ባለፈው ሳምንት በህንድ በሚካሄደው ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩያንግ የሚመራ ልኡክ እንደምትልክ መግለጿ ይታወሳል።
ባይደን እና ዥ ባለፈው አመት ነበር ኢንዶኔዥያ ባዘጋጀችው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ የተገናኙት።
በዚህ አመት አሜሪካ በቻይና የዲፕሎማቲክ ጉብኝት ብታደርግሞ የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ነው ያለው።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝደንት ዥ በህንድ ይገኛሉ ወይስ አይገኙም ተብሎ ለተነሳለት ቀጥተኛ ጥያቄ የማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ምላሽ አልሰጠም።
"ሊ ኪያንግ የቻይናን የልኡክ ቡድን በመምራት በህንዱ ስብሰባ ይካፈላሉ። ይህ ቻይና ትልቅ ግምት የምትሰጠው አለምአቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ነው" ብሏል የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ።
ነገርግን ዘገባዎች እንዲያመለክቱት ዥ ጅንፒንግ በህንዱ ስብሰባ ለመሳተፍ እቅድ የላቸውም ተብሏል።ይህ ዜና የተሰማው የቻይና እና ህንድ ግንኙነት ውጥረት ውስጥ በገባበት ወቅት ነው። ሀለቱ ሀገራት በሂማሊያ በኩል በሚገኘው ድንበራቸው በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ ገብተው ያውቃሉ። ባለፈው ሳምንት ቻይና አሩናቻል ፕሬደሽ ግዛት እና አክሳይ ተራራን የግዛቷ አካል አድርጋ በካርታ ላይ ማካተቷ ህንድን አስቆጥቷል።