ጆ ባይደን ኔታንያሁ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አላደረጉም ሲሉ ወቀሱ
ፕሬዝዳንቱ እስራኤል እና ሀማሳ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የሚጠይቅ የድርድር ሀሳብ ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል
የእስራኤል ተደራዳሪዎች ጠቅላይ ሚንስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ “ግትር” አቋም እያንጸባረቁ ነው በሚል ቅሬታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
ጆ ባይደን ኔታንያሁ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አላደረጉም ሲሉ ወቀሱ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት እያደረጉ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሃሪስ እና ከእስራኤል ተደራዳሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ዋሽንግተን በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ የተለያዩ ጥረቶችን ብታደርግም ስኬታማ መሆን አልቻለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ የድርድር ሂደቶቹ እንዲሳኩ በቂ ትብብር እያደረጉ አያደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ጠንካራ ግፊት ማድረጓን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ስድስት ታጋቾች በጋዛ ተገድለው መገኝታቸውን ተከትሎ በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ጠቅላይ ሚንስትሩ ከስልጣን እንዲነሱ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ተቀጣጥለዋል፡፡
ዋሽንግተን ለመጨረሻ ጊዜ ሁለቱን ተዋጊዎች ሊያስማማ ይችላል ያለችውን የተኩስ አቁም የስምምነት ሀሳብ ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ሳምንት እንደምታቀርብ አስታውቃ፤ ኔታንያሁ ይህ የመጨረሻ እድላቸው እንደሆነ አውቀው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ከአሜሪካዊያን ታጋች ቤተሰቦች ጋር ባደረጉት ውይይት መንግስታቸው ጦርነቱን ለማስቆም እና ተጋቾችን ለማስለቀቅ ጥረቱን መቀጠሉን ገልጸውላቸዋል፡፡
የተጋች ቤተሰቦች በበኩላቸው አሜሪካ በእስራኤል ላይ የተለየ ስልት ካልተጠቀመች ውጤቱ ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ቴልአቪቭ ላይ ጠንከር ያለ ጫና እንዲደረግባት ጠይቀዋል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ባሳለፍነው ቅዳሜ የተገደሉትን ታጋቾች ተከትሎ በባይደን አስተዳደር ላይ ከፓርቲው እየደረሰ የሚገኝው ጫና እየበረታ ነው፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ከስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት የጋዛውን ጦርነት ማስቆም እና ታጋቾችን ማስለቀቅ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ ነው፡፡
የባይደን አስተዳደር የሀማስ ሃላፊዎችን ለድርድሩ ፍሬያማ አለመሆን ተጠያቂ ሲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለስልጣናቱ ደግሞ የኔታንያሁ አዳዲስ ፍላጎቶችን ወደ ድርድሩ ማምጣት ለድርድሩ ውድቀት ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ፡፡
ከሳምንት በፊት የእስራኤል ተደራዳሪዎች ኔታንያሁ ድርድሩ እንዳይሳካ ዋነኛ እንቅፋት ሆነዋል ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
ተደራዳሪዎቹ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጦርነቱ “ፍጹም አሸናፊነትን” በመፈለግ በሚያንጸባረቁት “ግትር” ሀሳብ ድርድሩ ውጤት ርቆታል ብለዋል፡፡