ፕሬዝዳንት ባይደን ይፋ ያደረጉት አዲሱ “የጋዛ የተኩስ አቁም እቅድ” በውስጡ ምን ይዟል?
በሶስት ምዕራፎች የተከፈለው እቅዱ ከታጋቾች ልውውጥ ጦርነትን እስከማቆም የሚደርስ ነው
ሃማስ ባይደን ያቀረቡትን የጋዛ የተኩስ አቁም እቅድ በበጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በሶስት ምእራፎች የተከፈለ አዲስ የተኩስ አቁም አቅድ በዛሬው እለት ይፋ አደርገዋል።
“ጦርነቱ ማብቂያ ጊዜ ደርሷል” ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን አዲስ ያቀረቡት እቅድ በጋዛ ተኩስ ለማስቆም እና የእስራኤልታጋጆችን ለማስመለስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የመጀመሪያው ምእራፍ
“ለ6 ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ይደረጋል” ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ “በዚህ ምእራፍ የእስራኤል ጦር ሰው ከሚበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ይደረጋል፤ አዛውንቶች እና ሴቶችን ጨምሮ የተወሰኑ የእስራኤል ታጋቾች ይለቀቃሉ፤ በምትኩም በእስራኤል በእስር ላይ የሚገኙ ፍሊስጤማውያን ይለቀቃሉ፤ ፍሊስጤማውያን ወደ መኖሪያቸው እንደሚለሱ ይደረጋል፤ በየዕለቱ 600 የጭነት መኪናዎች ለጋዛ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ይደረጋል” ብለዋል።
ሁለተኛ ምእራፍ
ሁለተኛው ምዕራፍ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፤ በዚህኛው ምእራፍ እስራኤል እና ሃማስ ጦርነቱን በዘላቂነት ማቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይደራደራሉ ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ ንግግሩ እስከቀጠለ ድረስ የተኩስ አቁምም ይራዘማል ብለዋል።
ሶስተኛ ምእራፍ
ሶስተኛው ምእራፍ ለጋዛ ትልቅ የመልሶ ግንባታ እቅድ ያካትታል ሲሉም ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
ሃማስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አዲስ የተኩስ አቁም አቅድ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ባይደን ያቀረቡትን የጋዛ የተኩስ አቁም እቅድ በበጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል።
ሃማስ በመግለጫው፤ “በዘላቂ የተኩስ አቁም፣ የእስረኤል ጦር ማስወጣት፣ ተፈናቃዮችን ማስመለስ፣ እስረኞችን በማስለቀቅ እና በጋዛ መልሶ ግንባታ ዙሪየ በሚቀርብ ማንኛመውም እቅድ ላይ ገንቢ እና አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመወያየት ዝግጁ ነኝ” ብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ስምምነቶን የሚያቀርብ የተደራዳሪዎች ቡድን ማዋቀሩን የገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን ሁሉንም ታጋቾችን ማስመለስን እንዲሁም ሃማስን ጦር እና መንግስት ማውደምን ጨምሮ ጦርነቱ ግቡን ሳይመታ እንደማይቆም አስታውቋል።
የእስራኤል ሃማስ ጦርነት በፈረንጆቹ ጥምቅት 7 የሃማስ ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የጀመረ ሲሆን፤ አሁን ስምነተኛ ወሩን አስቆጥሯል።
ሃማስ በወቅቱ በድንገት በእስራኤል ላይ በከፈተው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲሞቱ፤ 250 እስራኤላውን ደግሞ በሃመስ መታገታቸውን እስራኤል በወቅቱ አስታውቃለች።
የሃማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለው የአጸፋ እርምጃ ከ35 ሺህ በላይ ፍሊስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው።
እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ በሚል በተለያዩ ግንባሮች ዘመቻዋን እንደቀጠለች ሲሆን የአሜሪካ የስለላ ተቋም ባወጣው ሪፖርት እስራኤል በ8 ወሩ ዘመቻ እስካሁን 35 በመቶ ያህል የሃማስ ታጣቂዎችን ብቻ ገድላለች ብሏል።
እንደ እስራኤል ባለስልጣናት መረጃ 128 ሰዎች አሁንም በሐማስ እጅ ታግተው የሚገኙ ሲሆን ታጋቾችን ለመልቀቅ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ድርድሮች እንደቀጠሉ ናቸው።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ወይም አይሲሲ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት እንዲሁም የሐማስ ወታደራዊ እና የፖለቲካ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ተጠይቋል።