76ኛው “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” እና የአሁኑ የጋዛ ጦርነት ምስስሎሽ
እስራኤል በ1948 ሀገር ሆና ስትመሰረት 700 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለችበት ክስተት “አል ናቅባ” ተብሎ ይጠራል
ወቅታዊው የጋዛ ጦርነት ዋነኛ አላማም ታጣቂዎችን መደምሰስ ሳይሆን ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ማፈናቀል ነው የሚሉ ክሶች ይቀርባሉ
እስራኤል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን በጅምላ ከቀያቸው ያፈናቀለችበት “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” 76ኛ አመት ዛሬ ታስቧል።
ፍልስጤማውያን ለነጻነት ትግላቸው መሰረት አድርገው የሚቆጥሩትን ክስተት በጦርነት ውስጥ ሆነው ነው ያሰቡት።
እስራኤል እንደ ሀገር ስትመሰረት ከቀያቸው ያፈናቀለቻቸው ፍልስጤማውያን ከ76 አመት በኋላም ከተደጋጋሚ ስደትና ግድያ አላመለጡም።
የ”አል ናቅባ” ክስተት እና የጋዛው ጦርነት
ፍልስጤም በክርስትና፣ እስልምና እና አይሁድ እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ስፍራ የሚቆጠር፤ በኦቶማን ቱርኮች ቁጥጥር ስር የነበረ አካባቢ ነው።
የኦቶማን ቱርክ ግዛት መፈራረስን ተከትሎ ብሪታንያ አካባቢውን ማስተዳደር መጀምሯ ይታወሳል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአይሁዳውያን ላይ ከተፈጸመው የጅምላ እልቂት በኋላ መጠለያ አገር ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገቡት አይሁዶች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድም በብሪታንያ ላይ ጫናው ይበረታል።
ይህም ፍልስጤም የሚደግፉ የአረብ ሀገራትና እስራኤልን ጦር ማማዘዙ ይታወሳል።
እስራኤል የመጀመሪያውን የአረብ - እስራኤል ጦርነት አሸንፋ ግንቦት 14 1948 እንደ ሀገር መመስረቷን ማወጇም አይዘነጋም።
በነጻነት አዋጁ ማግስትና ከዚያ ቀጥለው በተካሄዱ ጦርነቶች ከ700 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ከቀያቸው እንዲወጡ ያደረገችበት ክስተት በፍልስጤማውያን ዘንድ “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” እየተባለ ይጠራል።
ከ1948ቱ ጦርነት በኋላ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቀደመ ቤታቸው እንዲመለሱ ሳይፈቀድላቸው በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ዮርዳኖስ ስደተኛ እንዲሆኑ ተገደዋል።
ይህ ታሪካዊ ክስተትም የፍልስጤማውያን የነጻነት ትግል መሰረት ሆኗል።
ፍልስጤማውያን ከ76 አመት በፊት ያጋጠማቸው ታሪካዊ ክስተት አሁንም እንዳልቆመ ይናገራሉ።
የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ያለውን ጥቃት ሽሽት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ይህም ከ1948ቱ የ”አል ናቅባ” ክስተት በእጥፍ ጭማሪ ያለው ነው የሚሉት ፍልስጤማውያን፥ ጦርነቱ ቆሞ ወደቤታቸው ቢመለሱ እንኳን ለመኖሪያ እንዳይሆን መፈራረሱን ያነሳሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃም ጋዛን መልሶ ለመገንባት ቢያንስ 16 አመታት ያስፈልጋል ማለቱ አይዘነጋም።
እስራኤል ከ76 አመት በፊት ፍልስጤማውያንን ከቀያቸው አፈናቅላ እንደሀገር ከተመሰረተች በኋላ የመሬት ወረራዋ እንዳልቆመም ነው ተደጋግሞ የሚነሳው።
የ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት የፍልስጤማውያንን ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም፣ የሶሪያን የጎላን ኮረብቶች እንዲሁም የግብጽ ሲናይ በርሃን (በ1984 እስክትመልሰው ድረስ) በቁጥጥሯ ስር አስገብታለች።
እስራኤል ከአረቦች ጋር ያደረገቻቸውን አራት ታላላቅ ጦርነቶች የሚያወሱ ተንታኞች የጋዛው ጦርነት አላማ ሃማስን የመደምሰስ አላማ አለው ቢባልም ዋነኛ ትኩረቱ የመሬት ወረራ ነው ይላሉ።