የዓለም ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛዋ የራፋ ከተማ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም አዘዘ
ውሳኔው የተላለፈው በእስራኤል ላይ የዘርማጥፋት ክስ የመሰረተችው ደቡብ አፍሪካ ከጠየቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው
ፍርድ ቤቱ እስራኤል በግብጽ እና በጋዛ መካከል ያለውን የራፋ ማቋረጫ በመክፈት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንድታደርግ አዟታል
የዓለም ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዋ የራፋ ከተማ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም አዘዘ።
ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘርማጥፋት ክስ ሲመለከት የነበረው የአለም የፍትህ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) በዛሬው እለት ባስተላለፈው አስቸኳይ ውሳኔ እስራኤል በጋዛዋ የራፋ ከተማ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም አዟታል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያነበቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ንዋፍ ሳሌም እስራኤል በጋዛ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያሻሽል እርምጃ እንድትወስድ ካዘዛት ወዲህ በፍልስጤም ጋዛ ያሉ ሁኔታዎች እየተባባሱ ነው ብለዋል።
"የእስራኤል መንግስት በራፋ የሚያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ በአስቸኳይ ማቆም እና በፍልስጤሙ ታጣቂ በድን ላይ ውድመት ሊያስከትል የሚችልን ጥቃት ጨምሮ ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ አለባት" ብለዋል ሳሌም።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ እስራኤል በግብጽ እና በጋዛ መካከል ያለውን የራፋ ማቋረጫ በመክፈት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንድታደርግ አዟታል።
እስራኤል መርማሪዎች ወደተከበበችው ጋዛ እንዲገቡ እንድትፈቅድ እና ሁኔታዎችን በአንድ ወር ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከመላው አለም የተሰባሰቡ 15 አባላት ያሉት የዳኞች ቡድን ትዕዛዙን በሁለት ተቃውሞ በ13 ድጋፍ አጽድቆታል። ከእስራኤል እና ከኡጋንዳ የመጡ ዳኞች ትዕዛዙን ተቃውመውታል።
ውሳኔው የተላለፈው በእስራኤል ላይ የዘርማጥፋት ክስ የመሰረተችው ደቡብ አፍሪካ ከጠየቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
አይሲጄ በሁለት መንግስት መካከል የሚኖርን አለመግባባት የሚፈታ የተመድ አካል ነው።
ፍረድ ቤቱ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የመጨረሻ እና አስገዳጅ ቢሆንም ከዚህ በፊት ችላ ሲባሉ ቆይተዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ተግባራዊ የሚያደርግበት አሰራር የለውም።
ከወሳኔው በኋላ ውስን ቁጥር ያላቸው የፍልስጤም ደጋፊዎች "ነጻ ፍልስጤም" እያሉ የፍልስጤምን ሰንደቅ አላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
በጋዛ እያደረገችው ያለውን ዘመቻ ራስን የመከላከል እርምጃ ነው የምትለው እስራኤል የሚቀርብባትን የዘርማጥፋት ክስ አትቀበለውም።
የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ከውሳኔ ዋዜማ እንደተናገሩት" እስራኤልን ዜጎቿን ከመከላከል እና ሀማስን ከማጥቃት የሚያግዳት ምድራዋ ኃይል የለም" ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል፣ ሀማስ በፈጸመው ጥቃት 253 ማገቱን እና 1200 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ በጋዛ እያካሄደችው ባለው ጥቃት ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስጣን ገልጸዋል።