የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ጠየቁ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው የፍልስጤም ሉአላዊ ሀገርነት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል
የቻይና አረብ የትብብር ጉባኤ በቤጂንግ ሲጀመር የጋዛው ጦርነት ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል
በመካከለኛው ምስራቅ የአሸማጋይነት ሚናዋ እንዲጎላ የምትፈልገው ቻይና በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ከአረብ ሀገራት መሪዎች ጋር እየመከረች ነው።
ዛሬ በቤጂንግ የተጀመረው የቻይና አረብ የትብብር ጉባኤም ዋነኛ አጀንዳው የጋዛ ጦርነት ሆኗል።
በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የአረብ ኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ፥ “የቻይና እና አረብ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ አለም ለተጋረጡባት ፈተናዎች የጋራ መፍትሄ በምትሻበት ወቅት እየተካሄደ ነው” ብለዋል።
በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን ይበልጥ ማባባሱን በመጥቀስም ጦርነቱ አሳሳቢ የሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉን አብራርተዋል።
የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን ጦርነት ለማስቆም የቤጂንግ እና የአረብ ሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጋዛ ተኩስ ቆሞ የሰብአዊ ድጋፎች በፍጥነት እንዲደርሱ ብሎም ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ የሁለት መንግስታት መፍትሄ ተግባራዊ እንዲሆን የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው “የፍልስጤማውያንን ሰቆቃ ያበዛው ጦርነት መቋጭው ሳይታወቅ ሊቀጥል አይጋባም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የፍልስጤም ሉአላዊ ሀገርነት እንዲረጋገጥም ጥሪ አቅርበዋል።
“የሁለት መንግስታት መፍትሄ”ን የምትደግፈው ቤጂንግ በጋዛ ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 500 ሚሊየን ዩዋን (69 ሚሊየን ዶላር) ለመስጠት ቃል የገባች ሲሆን፥ በመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት በኩል ድጋፍ ለመላክም 3 ሚሊየን ዶላር መመደቧ ተገልጿል።
ቻይና የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ስትሰጥ እስራኤልን ስትቃወም መቆየቷ ይታወሳል።
የቤጂንግን አቋም የሚጋሩት የአረብ ሀገራት በፈረንጆቹ 2004 የመሰረቱት የቻይና አረብ የትብብር ፎረም በቤጂንግ ሲጀመር የግብጽ፣ ባህሬን እና ቱኒዚያ መሪዎችም እየተሳተፉ ነው።
ጉባኤው ከጋዛ ጉዳይ ባሻገር የአረብ ሀገራት እና ቤጂንግን የንግድ ትስስር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክርም ይጠበቃል።