አሜሪካ ሁለተኛዋን ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ከላከች ከአንድ ቀን በኋላ 2ሺ የባህር ኃይል ወታደሮችን ወደ እስራኤል መላኳን አስታውቃለች
አሜሪካ 2ሺ የባህር ኃይል ወታደሮቿን ወደ እስራኤል ልካለች
አሜሪካ ሁለተኛዋን ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ከላከች ከአንድ ቀን በኋላ 2ሺ የባህር ኃይል ወታደሮችን ወደ እስራኤል መላኳን አስታውቃለች።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ልሎይድ ኦስቲን ባለፈው ቅዳሜ ዩኤኤስ ኢሸንአወር የተሰኘች የጦር መርከብ ወደ ምስራቅ ሚዲትራኒያን ባህር መላኳን አስታውቀው ነበር።
ኢሸንአወር ቀድማ የተላከችውን ከአለም ግዙፍ የሆነችውን እና 75 የተለያዩ የጦር ጀቶችን መሸከም የምትችለውን ጀራልድ አር.ሮርድ የተሰኘችውን ተቀላቅላለች።
የባህር ኃይል ወታደሮቹ የተላኩት አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ኃይል ለማሳየት እና የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል።
አሜሪካ 2ሺ ወታደሮቿን ለመላክ የወሰነችው በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን በፍጥነት እያጠናከረች ባለችበት ወቅት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባይደን በሚቀጥለው ሮብዕ እስራኤልን ይጎበኛሉ።
የባይደን ጉብኝት ባልተጠበቀው የሀማስ ጥቃት 1300 ዜጎቿ ለተገደሉባት እና የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ አጋር ለሆነችው እስራኤል ድጋፍ ለማሳየት የታሰበ ነው ተብሏል።
እስራኤል የሀማስ ይዞታ የሆነችውን ጋዛን በመክበብ ያለማቋረጥ የአየር ድብደባ እያካሄደች ነው፣ በድብደባውም በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ባይደን ሀማስ በደቡባዊ እስራአል ድንበር ጥሶ በመግባት ያደረሰውን ጥቃት ባወገዙበት መግለጫቸው፣ አሜሪካ እስራኤል ራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን ሀሉ ማሟላቷን እንደምታረጋግጥ ተናግረዋል።