እስራኤልና ሃማስ በረመዳን ፆም መግቢያ ተኩስ ያቆማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ባይደን ተናገሩ
ኔታንያሁ በበኩላቸው በጋዛ የሚደረስ የትኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት በራፋህ የሚደረገውን ውጊያ አያስቆምም ብለዋል
እስራኤልና ሃማስ በተናጠል ከኳታር አደራዳሪዎች ጋር በዶሃ እያደረጉት ያለው ምክክር ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል
እስራኤልና ሃማስ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
የእስራኤልና ሃማስ አመራሮች ከኳታር እና አሜሪካ አደራዳሪዎች ጋር በተናጠል ግን በተመሳሳይ ከተማ (ዶሃ) እያካሄዱት ያለው ንግግር ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል።
እስራኤል እስከ ረመዳን ፆም መግቢያ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረሰ በራፋህ ጦርነት እጀምራለሁ ማለቷም ድርድሩ እንዲፈጥን ማድረጉ ተገምቷል።
"የብሄራዊ ደህንነት አማካሪዬ ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባችን ነግሮኛል፤ ያላለቁ ጉዳዬች ቢኖሩም እስከ ቀጣዩ ሰኞ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን።
የአሜሪካ አደራዳሪዎች እስከ መጋቢት 10 ድረስ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የታጋች እና እስረኞች ልወውጥ እንዲጀመር ግፊት እያደረጉ ነው።
እስራኤልና ሃማስ ግን ለተኩስ አቁም ድርድሩ መጓተት እርስ በርስ መካሰስና የጋዛው ጦርነት መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን የሚያሳዩ ንግግሮችን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የሃማሱ የፓለቲካ ቢሮ ሃላፊ ኢስማኤል ሀኒየህ ከኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር ከመከሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ በማድረግ ፍልስጤማውያንን መግደሏን ቀጥላለች ብለዋል።
"የተኩስ አቁም ድርድሩን የወንጀሏ መደበቂያ እንድታደርገው አንፈቅድም" ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ሀገራቸው የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ዝግጁ ብትሆንም ሃማስ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለድርድር የማይመጥኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኔቴንያሁ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ሃማስ ወደ እውነታው መምጣትና መወሰን አለበት" ሲሉ ተደሞጠዋል።
በጋዛ የሚደረስ የትኛው የተኩስ አቁም ስምምነት በራፋህ የሚደረገውን ውጊያ አያስቆምም ማለታቸውም ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት በፓሪስ አሁን ደግሞ በዶሃ እየተደረገ በሚገኘው ድርድር የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆነዋል።
እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ ሃማስ ባቀረበው ቅድመ ሁኔታ ዙሪያ አደራዳሪዎቹ ያሉት ነገር ባይኖርም ቴል አቪቭ የተለወጠ አቋም እንደሌላት አስታውቃለች።
በራፋህ መሽጓል ያለችውን ሃማስ ለመደምሰስ የያዘችው እቅድ ንፁሃን እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ነው የገለፀችው።
በኳታር ከረመዳን ፆም መግቢያ ጀምሮ የሚተገበር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም የፍልስጤማውያን ሰቆቃ በአጭር ጊዜ የሚቆም አይመስልም።