በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ በፓሪስ ምክክር እየተደረገ ነው
የእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ሃላፊ ከኳታር፣ ግብጽና አሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር እየተነጋገሩ መሆኑ ተገልጿል
በፓሪሱ ምክክር ኢስማአል ሃኒየህ በግብጽ በነበራቸው ቆይታ ይፋ ባደረጉት የሃማስ አቋም ዙሪያ የእስራኤል ምላሽ ይጠበቃል
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ያለመ ምክክር በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ እየተካሄደ ነው።
ትናንት በተጀመረውና ዛሬና ነገም ይቀጥላል በተባለው ምክክር ላይ የእስራኤሉ የስለላ ተቋም (ሞሳድ) ሃላፊ ከኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር በተናጠል ይመክራሉ።
የግብጹ አል ቃሄራ ቴሌቪዥን እንደዘገበው የፓሪሱ ምክክር የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊው ኢስማአል ሃኒየህ በግብጽ በነበራቸው ቆይታ ይፋ ባደረጉት የቡድኑ አቋም ዙሪያ የእስራኤል ምላሽ የሚጠበቅበት ነው።
እስራኤል በፍጥነት የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረሰ በረመዳን ጾም መጀመሪያ በራፋህ ጦርነት ለመክፈት ዝታለች፤ አሜሪካ በበኩሏ ሚሊየኖችን አደጋ ላይ የሚጥለውን እርምጃ ተቃውማለች።
ቴል አቪቭ በፓሪሱ ምክክር ዙሪያ እስካሁን ያለችው ነገር ባይኖርም ከቀደመ አቋሟ መለሳለስ አለማሳየቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
በየካቲት ወር መጀመሪያ በፓሪስ በተካሄደ መሰል ምክክር እስራኤልና አሜሪካ ያጸደቁት የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ መቅረቡ ይታወሳል።
ሃማስም ለዚህ ምላሽ የሚሆንና ለ135 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ማቅረቡ አይዘነጋም። የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ የሚወጡበትንና ታጋቾች የሚለቀቁበትን ሂደት ያመላከተው የሃማስ እቅድ ግን በኔታንያሁ “ቅዠት” ነው ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ለጦር ካቢኔው ባቀረቡት እቅድ በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም ሀገራቸው ወታደሮቿን እንደማታስወጣ ማመላከታቸው ተዘግቧል።
ሃማስም ሆነ በዌስትባንክ የሚገኘው የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛ ሰርጥ ምንም አይነት ሃላፊነት አይኖራቸውም ማለታቸውንም ነው ሬውተርስ ያወሳው።
ሃኒየህ በግብጽ በነበራቸው ቆይታ የቡድኑ አቋም አለመለወጡን የሚያነሱ ዘገባዎች የፓሪሱ ምክክርም ይዞት የሚመጣው አንዳች ነገር እንደሌለ እየጠቆሙ ነው።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ኦሳማ ሃምዳን በትናንትናው እለት በቤሩት በሰጡት መግለጫም “እስራኤል የያዘችው ግትር አቋምና ለአደራዳሪዎች የምትሰጠው አሉታዊ ምላሽ ስምምነት ላይ ለመድረስ አዳጋች ሁኔታ ፈጥሯል” ብለዋል።
“ኔታንያሁ ለታጋቾች መለቀቅ ደንታ የለውም፤ ይልቁንም ጉዳዩን ግቡን ማሳኪያ ካርድ አድርጎ እየመዘዘው ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
141ኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 30 ሺህ ገደማ ፍልስጤማውያን ህይወት ቀጥፎም በሰላማዊ ንግግርና ድርድር ሊቋጭ አልቻለም።
እስራኤል ሃማስ መሽጎበታል ባለችው ራፋህ የእግረኛ ጦር አስገብቼ እጀምረዋለሁ ያለችው ጦርነትም ከባድ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋቱ ከቀን ቀን እያየለ ነው።