ጆርዳን የእስራኤልም ሆነ የኢራን የጦር ሜዳ አትሆንም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስጠነቀቁ
"የአየር ክልላችን ጥሶ ህዝባችንን ለጥቃት ለሚያጋልጥ ለማንኛውም አካል እንደማንፈቅድ ለኢራን እና ለእስራኤል አሳውቀናል"ሲሉ የጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስጠንቅቀዋል
የሀማስ የፖለቲካ መሪ የሆነው ሀኒየህ ቴህራን ውስጥ ከተገደለ በኋላ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ዝታለች
የጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጆርዳን የእስራኤል ወይም የኢራን የጦር ሜዳ ልትሆን አትችልም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሚኒስተሩ ይህን ያሉት ባለፈው ሳምንት የሀማስ እና የሄዝቦላ መሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን እና አጋሮቿ በቀጣናው መጠነሰፊ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ባየለቀት ወቅት ነው።
"ለእስራኤል ወይም ለኢራን የጦር ሜዳ አንሆንም። የአየር ክልላችን ጥሶ ህዝባችንን ለጥቃት ለሚያጋልጥ ለማንኛውም አካል እንደማንፈቅድ ለኢራን እና ለእስራኤል አሳውቀናል"ሲሉ የጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሳኡዲው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"በአየር ክልላችን የሚያልፍን ማንኛውንም ነገር ወይም ለዜጎቻችን ስጋት ይሆናል ብለን በምናስበት ወቅት መትተን እንጥላለን።"
ባለፈው ሚያዝያ ወር በኢራን እና በእስራኤል መካከል የምትገኘው ጆርዳን ቴህራን ለመጀመሪያ ጊዜ ፈንጂ ድሮኖችን እና ሚሳይሎችን በቀጥታ ወደ እስራኤል ባስወነጨፈችበት ወቅት በራሪ አካላትን ማክሸፉን መግለጿ ይታወሳል።
ኢራን ያንን ጥቃት የፈጸመችው እስራኤል በሶሪያ የሚገኘውን ኢምባሲዋን እንደመታችባት ከገለጸች በኋላ ነው። ከዚህ ጥቃት በኋላ ግን የጆርዳን፣ የቱርክ እና የኢራቅ ባለስልጣናት፣ ኢራን ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት እያሳወቀቻቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የሀማስ የፖለቲካ መሪ የሆነው እስማኤል ሀኒየህ በሐምሌ መጨረሻ የአዲሱን የኢራን ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያኒ በዓለ ሲመት ለመታደም በሄደበት ቴህራን ውስጥ ከተገደለ በኋላ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ዝታለች።