ሃማስ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ መቀበሉ ተሰማ
የፍልስጤሙ ቡድን እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ የማትወጣ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት አልፈራረምም የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ማለዘቡም ተገልጿል
በኳታር የተጀመረው የእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ድርድር በቀጣዩ ሳምንት ይቀጥላል ተብሏል
ሃማስ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ መቀበሉ ተነገረ።
ቡድኑ የተኩስ አቁም ስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ከ16 ቀናት በኋላ ወታደሮችን ጨምሮ የእስራኤል ታጋቾችን በሚለቅበት ሁኔታ ላይ ድርድር ለመጀመር ነው የተስማማው።
ሬውተርስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን የቡድኑን አመራር ጠቅሶ እንደዘገበው፥ የፍልስጤሙ ቡድን እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ካልወጣችና ዘላቂ ተኩስ አቁም ካልተደረሰ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አልፈራረምም የሚለውን ቅድመ ሁኔታውን ስርዟል።
አሜሪካ ያቀረበችውና ለስድስት ሳምንታት በሚቆዩ ምዕራፎች የሚተገበረው የተኩስ አቁም ስምምነት የዘጠኝ ወራቱን ጦርነት የሚያስቆም ከሆነ ድርድሩን ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ገልጿልም ነው የተባለው።
ለዚህ የሃማስ በጎ ምላሽ ከእስራኤል በኩል ተመሳሳይ ፍላጎት ከሌለ ግን ጦርነቱ መቀጠሉ እንደማይቀር ነው የሃማስ አመራሮች ነግረውኛል ብሎ ሬውተርስ የዘገበው።
የእስራኤል የድርድር ቡድን አባል ናቸው የተባሉ ግለሰብም በአሁኑ ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ከእስካሁኑ የተሻለ እድል መኖሩን ተናግረዋል።
በሃማስ በኩል የታየው የአቋም መለሳለስ ስምምነት እንዲደረስ በሩን ይከፍታል የሚል እምነት ፈጥሯል።
ከ37 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት እንዲቆም በኳታር፣ ግብፅ እና አሜሪካ አደራዳሪነት ሲካሄዱ የቆዩ ድርድሮች በህዳር ወር ከተደረሰው ስምምነት ውጭ ስኬታማ አልነበሩም።
ለዚህም ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሚደረገው የተኩስ አቁም ድርድር የኔታንያሁ አስተዳደር ወደ ጋዛ የላካቸው ወታደሮች ሙሉ በሙሉ የሚወጡበትን ሂደት ማካተት አለበት የሚለው የፀና አቋሙ አንዱ ምክንያት ነበር።
እስራኤል በበኩሏ የሃማስ ታጣቂዎችን የነገ የደህንነት ስጋቴ እንዳይሆኑ አድርጌ ካልደመሰስኩ ከጋዛ አልወጣም ማለቷና ድብደባዋን መቀጠሏ የተኩስ አቁም ድርድር ጥረቶቹን ፈትኗል።
ከቀናት በፊት በኳታር መዲና ዶሃ ድርድሩን ዳግም ለመጀመር በተደረገው ምክክር ከሃማስ በኩል መለሳለስ መታየቱ ግን የጋዛን ውድመትና የፍልስጤማውያንን ሰቆቃ ጋብ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ሊደረስ ይችላል የሚል ተስፋን አጭሯል።
የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ሃላፊ በዶሃ ከአደራዳሪዎች ጋር ያደረጉትን ምክክር አጠናቀው ወደ ቴል አቪቭ መመለሳቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፥ ድርድሩ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ከአራት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው አሜሪካ በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረስ በአጋሯ እስራኤል ላይ ጫና እያደረገች ነው ተብሏል።