ኢራን አውሮፓውያን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትታቀብ ያቀረቡላትን ጥሪ ውድቅ አደረገች
ኢራን "መቼ" እና "እንዴት" የሚለውን ባትገለጽም፣ በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሯ የማይቀር እንደሆነ ግልጽ አድርጋለች
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በቀጣናው ከፍተኛ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል
ኢራን አውሮፓውያን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትታቀብ ያቀረቡላትን ጥሪ ውድቅ አደረገች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ፈረሳይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትታቀብ ያቀረቡት ጥሪ "ፖለቲካዊ አመኬንዮን እና አለምአቀፍ የህግ መርሆችን የሚጥስ ነው።"
ሶስቱ የአውሮፖ ሀገራት በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ ባለፈው ወር የሀማስ የፖለቲካ መሪ ሀኒየህ በቴህራን መገደሉን ተከትሎ ኢራን እና አጋሮቿ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቀናኒ "ሶስቱ ሀገራት ያወጡት መግለጫ ጽዮናዊው አገዛዝ የፈጸመውን ወንጀል ሳይቃወም፣ ኢራን ሉአላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ ሲጣስ ምላሽ እንዳትሰጥ ይጠይቃል" ብለዋል።
ቀናኒ እንደገለጹት ቴህራን እስራኤልን ለመመከት መዘጋጀቷን እና ፓሪስ፣ በርሊን እና ለንደን "የጋዛውን ጦርነት እና ጦርነት ናፋቂዋን እስራኤልን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቃወሙ" ጥሪ አቅርባለች።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሀማስ መሪ ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በአዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ፔዝስሽኪያኒ በዓለ ሲመት ላይ ከታደመ በኋላ ባረፈበት ክፍል እና የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር ደግሞ በቤሩት ከተማ ዳርቻ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ሀማስ እና ኢራን ግድያውን ፈጽማለች በሏት እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።
ኢራን "መቼ" እና "እንዴት" የሚለውን ባትገለጽም፣ በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሯ የማይቀር እንደሆነ ግልጽ አድርጋለች።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በቀጣናው ከፍተኛ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የተፈጠረው ውጥረት እንደሚያሳስባት የገለጸችው አሜሪካም ሚሳይል የሚሸከሙ የጦር መርከቦቿን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳን ይፋ አድርጋለች።