ባይደን የቀረቡበትን ክሶች ላመነው ልጃቸው ሀንተር ምህረት አደረጉ
በልጃቸው የክስ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም ሲሉ የቆዩት ፕሬዝዳንቱ "ሀንተር ልጄ በመሆኑ ብቻ ተመርጦ ፍትሃዊ ያልሆነ ክስ ተመስርቶበታል" ብለዋል
ትራምፕ በበኩላቸው የባይደን የምህረት ውሳኔን አድሏዊና "የፍትህ ስርአቱን መግደል ነው" ሲሉ ተቃውመውታል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተለያዩ ክሶች ለቀረቡበት ልጃቸው ሀንተር ባይደን ምህረት አደረጉ።
ከታክስ ክፍያ እና የጦር መሳሪያ ግዥ ጋር በተያያዘ የቀረበበትን ክስ ያመነው ሀንተር ከሁለት ሳምንት በኋላ የቅጣት ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ሲጠበቅ ነው ባይደን በምህረት አዋጁ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት።
ፕሬዝዳንቱ በልጃቸው የክስ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ ሲገልጹ ቢቆዩም ከዋይትሃውስ ከመውጣታቸው በፊት፥ ሀንተር ከጥር 1 2014 እስከ ታህሳስ 1 2024 ባሉት ጊዜያት ፈጽሞታል በሚል በሚቀርብበት ክስ ተጠያቂ እንዳይሆን ወስነዋል።
"በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት በሚል ልጄ በመሆኑ ብቻ በልዩነት ኢፍትሃዊ የሆነ ክስ እየቀረበበት እንኳን ቃሌን ጠብቄ ቆይቻለሁ፤ ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ ሰው ይህን ይረዳዋል" ያሉት ባይደን የፖለቲከኞች ኢላማ ሆኗል ያሉትን ልጃቸውን በምህረት ነጻ አድርገዋል።
ከአደንዛዥ እጽ ሱስ በማገገም ላይ የሚገኘው ሀንተር ባይደን በመስከረም ወር 2024 በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ታክስ ማጭበርበር የቀረበበትን ክስ ማመኑ ይታወሳል። በዚህ ክስም ታህሳስ 16 2024 የሚተላለፍበት የቅጣት ውሳኔ ይጠበቅ ነበር።
"በሱስ ውስጥ በነበርኩበት የጨለማ ጊዜ ውስጥ ያጠፋኋቸውን ጥፋቶች አምናለሁ፤ ሃላፊነትም እወዳለሁ፤ ጥፋቶቹ በህዝብ ፊት ያዋረዱኝና ቤተሰቦቼን ጭምር ያሳፈሩ ናቸው" ያለው ሀንተር፥ ምህረቱ ከፕሬዝዳንት አባቱ የተሰጠው በመሆኑ በዋዛ እንደማያየው ተናግሯል።
በቀጣይ ህይወቱ በሱስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ህይወት ለማስተካከል ብርቱ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል መግባቱንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ሪፐብሊካኖች ግን የባይደንን ውሳኔ ተቃውመውታል። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም አድሏዊ ነው ያሉት የባይደን ምህረት የፍትህ ስርአቱን እንደመግደል ይቆጠራል ብለዋል በትሩዝ ሶሻል ሚዲያቸው።
ምህረት የሚገባቸው ከጥር ወር 2021ዱ የካፒቶል አዳራሽ ነውጥ ጋር በተያያዘ ለአመታት በእስር የሚገኙ ደጋፊዎቻቸው መሆናቸውን በመጥቀስም የባይደን ቤተሰቦች በሙስና የተጨማለቁ ናቸው ሲሉ ከሰዋል።
ቤዩ የተሰኘው ልጃቸው በ2015 በካንሰር የሞተባቸው ፕሬዝዳንት ባይደን ግን ከታክስ፣ አደንዛዥ እጽ እና ያለፈቃድ ከተገዛ የጦር መሳሪያ ጋር ሪፐብሊካኖች የሚያብጠለጥሉትን ልጃቸውን ተከላክለውለታል።
ግብር ያልከፈሉ ሰዎች ወለድና ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል እንጂ እንዴት ክስ ይመሰረትበቸዋል? ሲሉ የሚጠይቁት ባይደን "ሀንተርን ለመስበር የሚደረግ ጥረት እኔንም የሚነካ ነው፤ ጅምሩ በዚህ የሚቆም ስላልሆነ በቃ ብያለሁ" ብለዋል።
"አሜሪካውያን አባት እና ፕሬዝዳንት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ለምን እንደሆነ እንደሚረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም አብራርተዋል።