ባይደን እና ትራምፕ በመጀመሪያ የዋይት ኃውስ ግንኙነታቸው በምን ጉዳዮች መከሩ?
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት፣ መካለኛው ምስራቅና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው
ትራምፕ እና ባይደን የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ የተለያየ አቋም አንጸባርቀዋል
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመራጩን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በዋይት ኃውስ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዚሁ ወቅትም ዶናልድ ትራምፕን “እንኳን በድጋሚ ተመልሰው መጡ” በማለት በነጩ ቤተ መንግስት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የረጅም ጊዜ ተቀናቃኝ የሆኑት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወይት ኃውስ ቆይታቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለ2 ሰዓታት የቆየ ውይይት ማድረጋቸውም ነው የተነገረው።
ባይደን እና ትራምፕ በመጀመሪያ ውይይታቸው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትና የመካለኛው ምስራቅ ጉዳይና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከተነሱ ጉዳዮች መካከል መሆናውን ዋይት ኃውስ አስታውቋል።
እንዲሁም ወሳኝ ብሆኑ በሀገራዊ ደህንነት እና የሀገር ውስጥ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በሀገሪቷ እና በአለም ዙሪያ እያጋጠሙ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውንም የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ኔን ፒር ተናግረዋል።
በውይይቱ ወቅት ስለ ሩሲያ ዩክሬን ጉዳይ የተነሳ ሲሆን፤ በዚህም ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ የተለያየ አቋም አንጸባርቀዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ዩክሬንን መደገፍ ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት የሚጠቅም መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ ጠንካራ አውሮፓን መፍጠር አሜሪካ ወደ ጦርነት ተገዳ እንዳትገባ ለመጠበቅ ይረዳል ማለታቸውን የዋይት ኃውስ ብሄራዊ ደህነንት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ተናግረዋል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት መናገራቸውን እና እንዴት የሚለውን ከማብራራት መቆጠባቸውምመ ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች ዙሪያ ሰፊ ጊዜ ወስደው መነጋገራቸውም ነው የተገለጸው።
ባይደን እና ትራምፕ በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ዙሪያም የተወያዩ ሲሆን፤ በዚህም ፕሬዝዳት ባይደን “ቃል እንደገባነው ሰላማዊ እና የተረጋጋ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር እናደርጋለን፤ ይህንን ለማረጋገጥም የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለዋል።
ከዲሞክራት የ2024 ፕሬዝደንታዊ እጩነት ራሳቸው ከማግለላቸው እና ምክትል ፕሬዝደንት ሀሪስ እንዲወዳደሩ ድጋፍ ከመስጠታቸው በፊት ከትራምፕ ጋር ሲወዳደሩ የነበሩት ፕሬዝደንት ባይደን የቀድሞውን እና የወደፊቱን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን በኦቫል ቢሯቸው ነው የተቀበሏቸው።
ይህ ተሰናባች ፕሬዝደንት የሚያደርጉት የተለመደ አሰራር ቢሆንም ባይደን በ2020 ባሸነፉበት ወቅት ግን ትራምፕ ይህን አላደረጉላቸውም ነበር።
ባይደን እና ትራምፕ ለአመታት አንደኛቸው ሌላኛቸውን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን በሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ላይም ሰፊ ልዩነት ያንጸባርቃሉ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትራምፕ የዲሞክራሲ ስጋት አድርገው የሚያይዋቸው ሲሆን የትራምፕ ደግሞ በባይደን ላይ አቅም የላቸው የሚል ትችት ያቀርቡባቸዋል።
ትራምፕ በ2020 ምርጫ የተሸነፉት ድምጽ ተሰርቀው እንደሆነ ያምናሉ።