የ81 አመቱ አዛውንት በቅርቡ በተካሄደው የአሜሪካ የምርጫ ክርክር ባሳዩት አፈጻጸም ከእጩነት እንዲነሱ የሚጠይቁ ደምጾች በርትተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና የ2024ቱ ምርጫ የዴሞክራት እጩ ጆ ባይደን ራሳቸውን ከእጩነት እንዲያገሉ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም በጥሩ አካላዊ እና አዕምራዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ በእምቢታቸው ጸንተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ከሚፈጽሙት ስህተት ባለፈ በቅርቡ በተካሄደው የመጀመርያ ዙር የምርጫ ክርክር ሀሳባቸውን በተገቢው መንገድ ለመግለጽ ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በክርክሩ በተቀናቃኛቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብልጫ እንደተወሰደባቸው በመግለጽ የዴሞክራት ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ፕሬዝዳንቱ ከእጩነት እንዲነሱ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በትራምፕ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ የሪፐብሊካኑ እጩ ያላቸውን ተቀባይነት እና ድጋፍ ሲጨምረው በአንጻሩ የ81 አመቱ አዛውንት ባይደን በሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ ጫናዎች እንዲበረቱባቸው አድርጓል፡፡
ባይደን ከእጩነት ራሳቸውን እንዲያነሱ በተለያዩ መድረኮች እና መገናኛ ብዙሀን በተጠየቁ ጊዜ ያስቀመጧቸው 4 ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
1.መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት
ፕሬዝዳንቱ ለማስተዳደር ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኛ ጆርጂ ስቴፋኖፖሎስ ትራምፕን ለማሸነፍ ትክክለኛው ሰው ነኝ ብለው ካላሰቡ ከዴሞክራት እጩነት ራስዎን ያገላሉ ሲል ለጠይቃቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “እግዝያብሔር ራሱ ይህን ካልነገረኝ በቀር ከእጩነት አልነሳም” ብለዋል፡፡ ይህም ፕሬዝዳንቱ በእጩነት ለመቆየት የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው ያመላከተ ሆኗል።
2. ተጨባጭ ማስረጃ
ባይደን በምርጫው በእርግጠኝነት እንደሚሸነፉ የህዝብ አስተያየቶች እና የጥናት ውጤቶች ይቅረቡልኝ ማለታቸው በእጩነት ለመቆየት ካስቀመጧቸው ምክንያቶች መካከል ሁለተኛው ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አመታዊ ጉባኤ መዝጊያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ካማላ ሃሪስ ትራምፕን ለማሸነፍ ትክክለኛዋ ሰው መሆኗን ካመኑበት ከእጩነት ይወጣሉ ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
በምላሻቸው በፍጹም ያሉት ፕሬዝዳንቱ “እስካሁን የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች በምርጫ የማሸነፍ እኩል እድል እንዳለኝ የሚያመላክቱ ናቸው ይህን የሚቀለብሱ የህዝብ ድምጽ እና ጥናቶች ከቀረቡ የተጠየቀውን ላደርግ እችላለሁ” ነበር ያሉት፡፡
3. አሳዛኝ አደጋ
በቅርቡ በዲትሮይት ከሚገኘው ኢንተርቴይመንት ኔትወርክ ከተባለ ሚዲያ ጋር የነበራቸውን የቃለ መጠይቅ ቆይታ በማጠናቀቅ ላይ ሳሉ ጋዜጠኛው በመዝጊያ ጥያቄው በድምጽ መስጫ ቀን ላይ እንደምንመለከትዎት መቶ በመቶ እርገጠኛ ነዎት? ሲል ጠይቋቸው ባይደንም “በባቡር ካልተገጭሁ አዎ 100 በመቶ እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ መልሰዋል፡፡
4. የጤና እክል
ባይደን በተለያዩ ጊዜ ከእጩነት ሊነሱ እንደሚችሉ በተጠየቁ ጊዜ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተለያዩ ናቸው፡፡
በቅርቡ በተመሳሳይ የቢኢቲው ጋዜጠኛ ኤድ ጎርደን ይህኑ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር። ፕሬዝዳንቱም ምንአልባት የጤና እክል ካጋጠማቸው እና ማስተዳደር በማይችሉበት ሁኔታ መሆናቸውን የሚያስረግጥ የጤና እክል ከተፈጠረባቸው ለአዲስ እጩ መንገዱን እንደሚከፍቱ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ በስልጣን ላይ ያሉ በእድሜ ትልቁ የመጀመሪያው መሪ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ጆ ባይደን ከምርጫ ክርክሩ በፊትም የሚፈጽሟቸው አወዛጋቢ ስህተቶች ለመሪነት ብቁ አይደሉም የሚሉ ተቃውሞዎች እንዲነሱባቸው እያደረገ ነው።
ባይደን ካስቀመጧቸው አራት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንድኛው እውን የሆነ ይመስላል። በትላንትናው እለት በላስ ቬጋስ ኔቫዳ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በኮቪድ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
የሚገኙበት የጤና ሁኔታ በእጩነት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው ስለመሆኑ እና አለመሆኑ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡