ሃማስ ለእስራኤል የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው
እስራኤል በጋዛ ለ40 ቀናት ተኩስ አቁማ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚያስችል የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ አቀረበች።
ትናንት በካይሮ ከግብጽና ኳታር አደራዳሪዎች ጋር በቀረበው የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ዙሪያ የተወያየው የሃማስ ልኡክ የሚሰጠው ምላሽ እየተጠበቀ ነው።
የፍልስጤሙ ቡድን በሁለት ቀናት ውስጥ በተኩስ አቁም ምክረሃሳቡ ላይ ምላሹን እንደሚሰጥ ነው የግብጽ የደህንነት ምንጮቹን ጠቅሶ ፍራንስ 24 ያስነበበው።
የተኩስ አቁምና የታጋቾች ማስለቀቅ ምክረሃሳቡ በሃማስ በኩል ተቀባይነት አግኝቶ በቀናት ውስጥ ሁለተኛው የተኩስ አቁምና የታጋች እስረኞች ልውውጥ ስምምነቱ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ ተናግረዋል።
ከጋዛ ጋር የምትዋሰነው ግብጽ በድንበሯ አቅራቢያ በራፋህ እስራኤል ልትጀምረው ያሰበችው የምድር ውጊያ አሳሳቧታል።
በዚህም የተኩስ አቁም ድርድሩ በፍጥነት እንዲካሄድ እያደረገች ነው ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በስልክ ሲወያዩ ካይሮ የተቻላትን ሁሉ ጫና አድርጋ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲፈረም ጥሪ ማቅረባቸውን ዋይትሃውስ አስታውቋል።
ባይደን ከኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋር ሲመክሩም እስራኤላውያን ታጋቾች አለመለቀቃቸው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ፈጥሯል ነው ያሉት።
በመሆኑም የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫዋ ዶሃ ቡድኑ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ እንዲቀበል ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ ጠይቀዋል።
ሃማስ ስለትናንቱ የካይሮ ድርድርና አዲሱ የእስራኤል የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።