ብሊንከን ከአረብ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ለመምከር ሪያድ ገቡ
የሚኒስትሮቹ ምክክር ከጋዛው ጦርነት በኋላ በሰርጡ ሊኖር በሚችለው አስተዳደርና የመልሶ ግንባታ ስራዎች ላይ ያተኩራል ተብሏል
ሃማስ ለእስራኤል የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ዛሬ በግብጽ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሰባተኛ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ነው።
ሚኒስትሩ ከአምስት የኣአረብ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ለመምከር ዛሬ ሳኡዲ አረቢያ ገብተዋል።
ብሊንከን ከአረብ ኤምሬትስ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ዮርዳኖስ እና ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሪያድ የሚያደርጉት ምክክር በጋዛ ከጦርነቱ በኋላ ምን አይነት አስተዳደር ይዋቀር በሚለው ዙሪያ ያተኩራል ተብሏል።
አሜሪካ ሃማስ ሙሉ በሙሉ መደምሰስ አለበት የሚለውን የእስራኤል አቋም ብትደግፍም እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ዳግም እንድትቆጣጠር ግን እንደማትፈልግ ስትገልጽ ቆይታለች።
አለማቀፍ እውቅና ያለውን የፍልስጤም አስተዳደር ያካተተ እና የአረብ ሀገራት ድጋፍ ያለው አስተዳደር እንዲመሰረትም ትፈልጋለች።
የሰብአዊ ድጋፍ የሚገባበት መንገድን ማስፋት እና የፈራረሰችውን ጋዛን መልሶ ለማቋቋም ከአውሮፓ ሀገራት ጋር በትብብር ሊሰራ የታሰበውን ስራ በተመለከተም ውይይት ይደረጋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሳኡዲ አረቢያ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ የጀመሩት ጥረትን በተመለከተም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ እንደሚመክሩ ነው የተገለጸው።
የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ሲያድሱ እስራኤል ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ዋሽንግተንም ጫና እንደምታደርግ ስምምነት ቢኖርም ኔታንያሁ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገውታል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሰባት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰባተኛ ጉብኝታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ብሊንከን የጋዛውን ጦርነት የሚያስቆምና ታጋቾችን የሚያስለቅቅ መፍትሄ አላገኙም።
ሚኒስትሩ የሪያድ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ እስራኤልና ዮርዳኖስ ያመራሉ የተባለ ሲሆን፥ እስራኤል በራፋህ ልትጀምረው ባሰበችው ጦርነት ዙሪያ የአሜሪካን አቋም ለኔታንያሁ አስረግጠው እንደሚናገሩም ተገልጿል።
በሌላ ዜና ሃማስ ለእስራኤል የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ዛሬ በግብጽ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር፥ “እስራኤል አዲስ መሰናክል እስካልፈጠረች ድረስ መልካም ነገሮች ነው ያሉት፤ በአዲሱ እቅድ ዙሪያ ያቀረብነው የተለየ ጉዳይ የለም” ማለታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
በካይሮው ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ እስራኤል በጋዛ ልትጀምረው ያሰበችውን ጦርነት “ልታቋርጠው” እንደምትችል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ገልጸዋል።
ቴል አቪቭ በራፋህ በይፋ የእግረኛ ጦሯን ባታስገባም በየቀኑ የምትፈጽመው የአየር ድብደባ የፍልስጤማውያንን ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል።